Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ስራ ላይ እንዲውል ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ሁለት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በብሄራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ላይ ባደረገው ውይይት፥ ዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ የንግድ ትስስር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

የንግድ ትስስሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መተማመን ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

በዚህ ረገድ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችል፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅምን ለማጎልበት እንዲሁም በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንዲቻል በዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደብ እንዲስፋፋና የሎጀስቲክ አገልግሎት እንዲቀላጠፍ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ስለሆነም ምክር ቤቱ በብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቀቂ ፖሊሲ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዲመሰረቱ የሚያስችል ፖሊሲ መሆኑን በማረጋገጥ ግብዓቶችን በማከል በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ነው የተገለጸው፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው በኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ መምከሩንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ አስተማማኝ የዲጂታል የመታወቂያ ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች እና በኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚገባ እንዲታወቁ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከማሳለጥ እና ከማቅለል ባለፈ የአገልግሎቶችን ተአማኒነት የሚያጎለብት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል ወጥ፣ አስተማማኝና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ የመታወቂያ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያለው፡፡

በዚህ መሰረትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ግብዓቶችን በማከል እንዲፀድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.