Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተዘጋጅቶ በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ነው፡፡
የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አስፈጻሚ ተቋማት ከተሰጣቸው ስልጣንና ተግባራቸው ጋር የሚመጣጠን የሰው ሃይል እንዲኖራቸው የሚያስችል የአደረጃጀት ማሻሻያ ማድረጋቸውን ተከትሎ በቀጣይ ሊፈጸሙ ስለሚገባቸው አቅጣጫዎች በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ስለኢንቨስትመንት ማበረታቻ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ የግሉ ዘርፍ ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ ዘርፉ ያለውን ሀብት መንግሥት ትኩረት በሚሰጣቸው የልማት መስኮች ላይ በማዋል ለኢኮኖሚ ዕድገት ተገቢውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችል የሚያበረታቱ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የውጭ ካፒታል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በአጠቃላይም ለማህበራዊ ኑሮ መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችልበትን መሠረት መጣል የሚገባ መሆኑን ከግምት በማስገባት እንዲሁም የተሰጠው ማበረታቻ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ የሚያስችል የክትትል ሥርዓት የሚዘረጋ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ግብዓቶች በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በጉምሩክ ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የአገራችንን የወጪና የገቢ ንግድ ሥርዓት ከሚመሩ ሕጎች መካከል የጉምሩክ መጋዘን አስተዳደርን እና የጉምሩክ አስተላላፊዎችን በሚመለከት የወጡ ደንቦች ይገኙበታል፡፡
እነዚህን ደንቦች በአንድ በማጠቃለል ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም፣ በአገራችን እያደገ የመጣውን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደግፍ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ፣ በስራ ላይ ካለው የጉምሩክ አዋጅ ጋር የሚጣጣም ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ከዛሬ ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
ቀጥሎ ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣንን ስልጣንና ተግባር እና አደረጃጀት ለመወሰን በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የፌደራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ 1263/2014 መሰረት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ መብትና ግዴታዎች እንዲተላለፉለት የተደረገ በመሆኑና በተሻለ አቅም የቁጥጥር ስራውን እንዲመራ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶች በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.