Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 476 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 476 ቢሊየን ብር እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።
 
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ባካሄደው 84ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
 
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በ2013 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ነው፡፡
 
በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 133 ቢሊየን 321 ሚሊየን 561 ሺህ፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 160 ቢሊየን 329 ሚሊየን 788 ሺህ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 176 ቢሊየን 361 ሚሊየን 602 ሺህ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 6 ቢሊየን በጠቅላላ ብር 476 ቢሊየን 12 ሚሊየን 952 ሺህ 445 እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ በጀት ምክር ቤቱ ከተወያየበት በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
 
የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ደንብ ሁለተኛ አጀንዳው ነበር፡፡
 
የኮቪድ 19 በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የግል ድርጅቶች ከሐምሌ 2007 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2012 ድረስ ባልተከፈለ የጡረታ መዋጮ ላይ ሊከፈል የሚገባውን መቀጮና ወለድ ሙሉ በሙሉ እንዲነሣ፤ የሚፈለግባቸውን ዕዳ ከከፈሉ በዕዳ ምክንያት የተያዙ ንብረቶችን ለድርጅቶቹ ለመመለስ የሚያስችሉ ተጨማሪ ርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ አቅርቧል፡፡
 
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
 
ሌላው የምክር ቤቱ የመወያያ ጉዳይ የኮቪድ-19ኝ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጡ የአስቸኳይ ጊዜ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ የተመለከቱ የትራፊክ ጥሰቶች በተፈጸሙ ጊዜ የሚጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው።
 
ምክር ቤቱ አንዳንድ ማስተካከያዎች በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
 
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የተደረገ ለበረሃ አንበጣ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ላይ ሲሆን በብድር የተገኘው ገንዘብ የበረሃ አንበጣ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱ በተጨማሪ ከወለድ ነጻና በረዥም ጊዜ የሚከፈል በመሆኑ የብድር ስምምነቱ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
 
በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተመለከተው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረቡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ነው፡፡
 
አራቱ ስምምነቶች ከሩዋንዳ መንግሥት እና ከጂቡቲ ሪፐብሊክ ጋር የተደረጉ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነቶች እና በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነቶች ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ናቸው።
 
ምክር ቤቱ ስምምነቶቹን ተቀብሎ ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
 
ሌላው ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የዕቃዎች የሽያጭ ውሎች ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡
 
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በዕቃዎች ዓለም አቀፍ ሽያጭ ውሎች ግንኙነት ውስጥ የሚኖረውን ተቀባይነት ከፍ የሚያደርግ እና የንግድ ግንኙነቶችን የሚያሳልጥ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁን ም/ቤቱ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.