Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ም/ቤት በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ባካሄደው 81ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው በጉዳዮቹ ላይ መክሮ ውሳኔውን ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

መዚህም መሰረት፦

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሸንን (Electronic Transaction) ለመደንገግ በቀረበውረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።

ከዚህ በፊት በወረቀት መሰረት ተደርገው ሲፈጸሙ የነበሩ የግብይት እና የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ መስል ህጋዊ እውቅና አግኝተው ስራ ላይ እንዲውሉ የሚደርግ እንደዚሁም የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች የዲጂታል ኢኮኖሚው አካል መሆናቸውን መነሻ በማድረግ፤ አገራችን እነዚህን ዘርፎች የምትመራበት የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት በማስፈለጉ የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማዕከል ያደረገ የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው።

ሆስፒታሉ የተቀናጀ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ ተገልጋይ ተኮርና ተደራሽነት ያለዉ የአዕምሮ እና የአካል ሕክምና አገልግሎቶችን አቀናጅቶ የሚሰጥ ሆስፒታል ሆኖ እንዲቋቋም ለማስቻል በጤና ሚኒስቴር የቀረበ ረቂቅ ደንብ ሲሆን ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.