Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ቀናት ውስጥ የመመለስ ስራ ይጀመራል- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም ገመገመ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ “ከሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በምስል የተደገፈ የስራ አፈፃፀም ግምገማ አሂደናል” ብለዋል።

በግምገማውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሚሲዮኖች ቅንጅታዊ ትብብር ዜጎችን ወደ ሃገር የመመለስ ተግባር ዝግጅቱ በመጠናቀቁ፤ በውጭ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በ2 ቀናት ውስጥ የመመለስ ስራው እንደሚጀመር መረጋገጡን አስታውቅዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ በድንበር አካባቢ ተጨማሪ ትኩረት በመስጠት የለይቶ ማቆያ (ኳራንቲን) አገልግሎት እንዲጠናከር፤ ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የምርመራ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።

እንዲሁም የወረርሽኙ ስርጭት በአንፃራዊነት ከፍተኛ የሆነባቸው አካባቢዎች ተለይተው ጥብቅ ክትትል እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

በተመረጡ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮሮና-19 ወረርሽን በመከላከል እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ውጤት ኮሚቴው የተመለከተ ሲሆን፥ አሁንም በየተቋማቱ ከፍተኛ መዘናጋት እንዳለ ለመረዳት መቻሉንም ገልፀዋል።

“ከዚህ ባሻገር ቫይረሱ የተገኘባቸው ዜጎች ቁጥር ከቀን ቀን መጨመሩ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የጥንቃቄ መመሪያዎቹን በማስተዋል ተግባራዊ ማድረጋችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አደራ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.