Fana: At a Speed of Life!

የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾችን አብዝቶ መጠቀም የታዳጊዎችን የአዕምሮ ጤና ይጎዳል – ጥናት

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማህበራዊ የትስስር ገጾችን አብዝቶ መጠቀም በታዳጊዎች አዕምሮ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል አንድ ጥናት አመላከተ።

በእንግሊዝ የተደረገና ከሰሞኑ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀም ታዳጊዎችን ለአዕምሮ እድገት ወሳኝ ከሆኑ እንቅስቃሴዎች በማራቅ በአዕምሮ ጤናቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይገልጻል።

ጥናቱ እድሜያቸው ከ13 እስከ 16 ዓመት በሆኑ 10 ሺሕ ታዳጊዎች ላይ የተደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

በጥናቱ ማህበራዊ የትስስር ገጾችን በቀን ከሶስት ጊዜ በላይ የሚጠቀሙት ማህበራዊ የትስስር ገጾችን አዘውትረው የሚጠቀሙ በሚል ተለይተዋል።

ታዳጊዎቹ ከሥነ ልቦና፣ የግል ደህንነት፣ የህይወት እርካታ፣ ደስታ እና ከጭንቀት ጋር በተያያዘ ያሉበት ሁኔታ ተገምግሟል።

በጥናቱ ውጤት መሰረት በሁለቱም ፆታዎች ውስጥ በጣም በተደጋጋሚ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የሚጠቀሙት ከከፍተኛ የስነልቦና ጫና እና ጭንቀት ጋር ለተያያዘ ችግር እንደሚዳረጉ ተገልጿል።

ታዳጊዎቹ ማህበራዊ የትስስር ገጾችን አብዝተው መጠቀማቸው ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲርቁ፣ በቂ እንቅልፍ እንዳያገኙ እና በበይነ መረብ ለሚፈጸም ትንኮሳና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋልም ነው ያሉት።

ይህ መሆኑ ደግሞ የታዳጊዎቹን የአዕምሮ እድገት ጤንነት እንዲጎዳ በማድረግ ከፍ ያለ ጫና ይፈጥራልም ነው የሚሉት አጥኝዎቹ።

ይህ አጋጣሚ ደግሞ በታዳጊ ሴቶች ላይ ከፍ ያለ መሆኑንም አጥኝዎቹ ገልጸዋል።

የጥናት ቡድኑ አባላት በዋናነት ታዳጊዎቹ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚጋሩትና የሚያገኙት መረጃ ይዘት ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ እንዳለውም አስምረውበታል።

ምንጭ፦ edition.cnn.com/

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.