Fana: At a Speed of Life!

የማዕድንና ነዳጅ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የማዕድንና ነዳጅ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የማዕድንና ነዳጅ ዘርፍን በሳይንስ፣ በጥናትና ምርምር መደገፍ ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል።

ተቋማቱ የማዕድንና ነዳጅ ሐብቶችን በአግባቡ ለመጠቀምና ዓለም ዓቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ እና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ የዘርፉን ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥባቸው የትምህርት ክፍሎችን በተመረጡ የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ስር መክፈት እንዳለባቸው ተስማምተዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፥ የማዕድንና ነዳጅ ልማትን ለማፋጠን የሚረዱ የምርምርና የማሰልጠኛ ተቋማትን በየደረጃው ለሚደረገው የሰው ኃብት ልማት፣ አቅም ግንባታ ስልጠና እና ለሰልጣኞች በዘርፉ ኢንዱስትሪዎች የተግባር ልምምድ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ በዘርፉ በተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የልምድ ልውውጥና የስራ ትብብርን የመፍጠር፣ ከተቋማቱ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የዘርፉን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ የማዘጋጀት፣ የሚከፈቱ ትምህርትና ስልጠና ክፍሎች በሳይንስ ጥናትና ምርምር እንዲጎለብቱ ስልት የመንደፍ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልፀዋል።

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ለሚከፈቱ የትምህርትና ስልጠና ክፍሎች ፕሮግራም የመቅረጽ፣ የዘርፉን ባለሙያዎች በስልጠና የማብቃት፣ የልህቀት ማዕከላትን በማቋቋምና የምርምር ስራዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች የማድረስ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች እና ኢንዱስትሪዎች መካከል የስራ ትብብር እንዲፈጠር እና የሚዘጋጁ ስልጠናዎች፣ አውደ ጥናቶች፣ ሴሚናሮችና መሰል ሁነቶችን የማስተናገድ ስራዎችን ተቋማቸው እንደሚያከናውን መግለፃቸውን ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.