Fana: At a Speed of Life!

የማይካድራ የንጹሃን ዜጎች ጥቃት በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና “ሳምሪ” የወጣቶች ቡድን የተፈፀመ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማይካድራ የንጹሃን ዜጎች ጥቃት በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና “ሳምሪ” የወጣቶች ቡድን የተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ምርመራ በማድረግ የደረሰበትን ግኝት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በሪፖርቱም በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመው ጥቃት፣ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል መሆኑን አስታውቋል።

ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክት ስለሆነ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑንም ገልጿል።

በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው በአካባቢው የነበረው የሚሊሻና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር የፌደራሉን የሃገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩ ጭካኔ በተሞላበትና በግፍ መግደላቸውንና እንዲሁም ንብረት ማውደማቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን ባገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችልም ነው በሪፖርቱ ያመላከተው፡፡

ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ “በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢ ሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል” ብለዋል።

አክለውም ”የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.