Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች ለአፍሪካ ቀንድ ንግድን የሚያቀላጥፍ ፍኖተ ካርታ አፀደቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማቀላጠፍ ያግዛል የተባለ ፍኖተ ካርታ አፅድቀዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች የንግድ ፍኖተ ካርታውን አተገባበር ሁኔታን ለመገምገም እና ቀጠናዊ ውህደትን ለማጠናከር መወሰድ ስላለባቸው ፖሊሲዎች በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በፋይናንስ ፕሮጄክቶች አቅርቦት መሻሻል መታየቱን የገለፁ ሲሆን በቅርቡም ለተለያዩ ፕሮጄክቶች ማስፈፀሚያ የሚሆን የ325 ሚሊየን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ ጋር መፈራረማቸውን ገልፀዋል፡፡

የሀገራቱ የገንዘብ ሚኒስትሮችም የምስራቅ አፍሪካ የንግድ ትስስር ማጠናከሪያ ፍኖተ ካርታው ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፍ እንዲደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡

በፋይናንስ ሚኒስቴር የንግድና ቀጠናዊ ውህደት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ዘዴን በመጠቀም ፍኖተ ካርታውን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የጂቡቲ፣ የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን የገንዘብና ንግድ ሚኒስትሮች እንዲሁም የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ኢጋድን ጨምሮ ሌሎች አጋር አካላት  ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በፈረንጆቹ 2019 የተመሰረተ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተጀመረውን ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ዓለም ባንክ እና በአውሮፓ ህብረት በሚገኝ ድጋፍ በትብብር ለመስራት የተቋቋመ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.