Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ ጦር ዩክሬን ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ጠዋት ሩሲያ ኪየቭን ጨምሮ በተለያዩ የዩክሬን ወታደራዊ ቀጠናዎች የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟ ተሰማ፡፡

በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የመኖሪያ ቤት ሕንፃ እና መዋዕለ-ሕፃናት መውደማቸው ነው የተነገረው፡፡

በተጨማሪም በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን ጨምሮ በሰሜን እና ምዕራብ ዩክሬን በሚገኙ ሦስት ወታደራዊ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች ላይም ጥቃት መፈጸሟም ነው የተገለጸው።

ሩሲያ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን አከታትላ እየፈጸመች ያለው በስፔን ማድሪድ ከሚካሄደው የኔቶ ጉባዔ ጥቂት ቀናት በቀሩበት ወቅት ነው ተብሏል።

በኪየቭ ቢያንስ ስድሥት ፍንዳታዎች መሠማታቸውን የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን በማዕከላዊ ቼርካሲ ከተማ እና በካርኪቭ ግዛት የሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን የአይን ዕማኞች አስታውቀዋል።

አንድ የዩክሬን ዓየር ኃይል አዛዥ “ከ50 የሚበልጡ የዓየር፣ የባሕር እና የምድር ተምዘግዛጊ ሚሳዔሎች ወደ ሀገሪቷ እንደተወነጨፉ ገልጸው በዓየር መቃወሚያ ለመምታት መቸገራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በቡድን ሰባት አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ መክፈቻ ቀን መሆኑን ደግሞ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለቤላሩስ የ”ኢስካንደር-ኤም” ሚሳዔል እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

ቭላድሚር ፑቲን ይህን ያሉት በትናንትናው ዕለት ከቤላሩስ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር በበይነ-መረብ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት መሆኑን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

በጥቂት ወራት ውስጥ ሚሳዔሉን እልካለሁም ነው ያሉት ፑቲን፡፡

“ኢስካንደር-ኤም” የተሠኘው ሚሳዔል እስከ 500 ኪሎ ሜትር ድረስ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚመራ ሚሳዔል ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ የኒውክለር አረር ማስወንጨፍ ይችላል ነው የተባለው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.