Fana: At a Speed of Life!

የሩስያ ባህር ኃይል አዳዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን በቅርቡ እንደሚታጠቅ ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩስያ ባህር ኃይል አዳዲስ ሃይፐርሶኒክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚታጠቅ ፕሬዚዳንት ፑቲን አስታወቁ፡፡

በትልልቆቹ የሩስያ የወደብ ከተሞች ቅዱስ ፒተርስበርግ እና ክሮንሽታት ዛሬ በተካሄደው ዓመታዊ የባህር ኃይል ቀን በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፥ ክሩዝ ሚሳኤሎችን የታጠቁ የባህር ኃይሎች በሩሲያ የደህንነት ፍላጎት መሰረት ስምሪት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን አክለውም፥ “መታየት ያለበት ቁልፍ ነገር፥ የሩስያ ባህር ኃይል ሉዓላዊነታችንን እና ነፃነታችንን ለመድፈር የወሰነን ኃይል ሁሉ በብርሃን ፍጥነት ለመለከላከል የሚችል አቅም አለው።” ነው ያሉት።

አዳዲስ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ለሩሲያ ጦር ኃይሎች የማስታጠቅ ሥራው በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚጀምርም ነው የተናገሩት፡፡

የሩሲያ ቀድምት የባህር ኃይል የሆነው የአድሚራል ጎርሽኮቭ የጦር መርከብ ክፍለ ጦር እነዚህን አስፈሪ ክሩዝ ሚሳኤሎች ወደ ውጊያ ግዳጅ የሚያሰማራ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ባህር ኃይል እንደሚሆንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች በድምፅ ፍጥነት በዘጠኝ እጥፍ መወንጨፍ የሚችሉ ሲሆን ሩሲያ ባለፈው አመት ጀምሮ ሚሳኤሉን ለማበልፀግ በጦር መርከቦቿ እና በባህር ሰርጓጅ መርከቦቿ ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

በተጨማሪም ፑቲን የባህር ኃይል ፖሊሲ እና የባህር ኃይል መርከብ ቻርተር ድንጋጌዎችን በዕለቱ በፊርማቸው ማጽደቃቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን ያጸደቋቸው አዳዲስ የባህር ኃይል ድንጋጌዎች አሜሪካ ዋነኛ ተቀናቀኝና ተወዳደሪ መሆኗን በግልጽ የሚስቀምጡና ሩስያ ቁልፍ በሆኑት በአርክቲክና በጥቁር ባህር አካባቢዎች የባህር ኃይል የበላይነትን ለመያዝ ያላትን ብርቱ ፍላጎት ያሳያል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.