Fana: At a Speed of Life!

ለሰሜኑ ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚያደርስ የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነድ ፀደቀ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የሰላም ምክረ ሃሳብ ሰነድን አፀደቀ።

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ÷መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ እስካሁን የነበረውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ መወያየቱን አስታውቋል፡፡

ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲያደርግ መቆየቱ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ማወጅን ጨምሮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳትን፣ እስረኞችን መፍታት፣ የሰብዓዊ ድጋፍን የማሳለጥ እርምጃዎችን ወስዷልም ነው የተባለው።

የሰላም አማራጭን በዘላቂነት እውን ለማድረግ በተለይም የግጭት ሰለባ በሆኑ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪ ዜጎች በእለት ተእለት ኑሯችው እየገጠማቸው ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የመሰረተ ልማት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ስራ ለማስጀመር አስቻይ የሆነ ሁኔታ ለመፍጠር፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ መድረስ እንደሚገባ ኮሚቴው አጽንዖት ሰጥቶ ተወያይቷል።

ኮሚቴው ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እና ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶች መሰረት የሚጥል የምክረ ሃሳብ ሰነድ አጽድቋልም ተብሏል በመግለጫው።

ምክረ ሃሳቡ በፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ መወሰኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ውይይትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት ትብብር በመታገዝ በአጭር ጊዜ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ፥ የሰላም ምክረ ሃሳቡን በተመለከተ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት ይህ ተግባር በዛሬው እለት ተከናውኗል ነው የተባለው።

ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆንም አብይ ኮሚቴው የገለጸው።

የአፍሪካ ህብረትም የሰላም ውይይቱ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ፥ የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ወስኖ ንግግሩ እንዲጀመር ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

የሰላም አብይ ኮሚቴው ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው ንዑስ ኮሚቴዎች እና ተቋማት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ለሰላም አማራጩ እውን መሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሳየውን ድጋፍ በማድነቅ፣ ይህ ድጋፍ ተጥናክሮ እንዲቀጥልም የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከአፍሪካ ህብረት ጎን በመቆም የሰላም ጥረቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋትፅኦ እንዲያበረክት ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.