Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን ሀይል በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየተስፋፋ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር ጉዳይ ያላትን ልዩነት በዲፕሎማሲ ለመፍታት እየሰራች ቢሆንም የሱዳን ሀይል አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ውስጥ እየተስፋፋ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሱዳን ሀይል ስምምነቶችን ባለከበረ መንገድ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነው ብለዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላቋረጠ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀጠናውን የማተራመስ ፍላጎት በመኖሩ ችግሩ በንግግር ብቻ እንዲፈታ በትዕግስት እየሰራች መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ኃይሎች ጋር ጦርነት ብታደርግም ነጦርነት ትርፍ እንደሌለው ትረዳለች ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት እንዲገቡ በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩሶስተኛ ወገኖች ፍላጎት እንዳለ ገልፀው፤ ኢትዮጵያ የጦርነት አማራጭ እንደማትጠቀም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የጋራ ዕድገት እንጂ ጦርነት እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት።

በአንፃሩ ሱዳን በድንበር አካባቢ አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ነገሮች መፍትሔ የማያገኙ ከሆነ ግን ትዕግሥት ገደብ ይኖረዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከዚህ ባለፈም ግብፅ እና ሱዳን ሆን ብለው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲጓተት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት መፍትሔ እንዳያገኝ እየሰሩ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ጉዳዩ ከተቻለ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲያመራ ካልሆነም ቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እስከሚቀየር ድረስ የመጠበቅ አካሄድ እየተከተሉ ነው ስለመሆኑም አውስተዋል።

በአላዛር ታደለ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.