Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን የተቃውሞ ሰልፎች በወታደራዊ ክንፉ እና በሲቪል አስተዳደር መካከል ውጥረት ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን እየተካሄዱ ያሉት ለሁለት የተከፈሉ የጎዳና ላይ ሰልፎች በሽግግር መንግስቱ ወታደራዊ ክንፍ እና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ እንዲል ማድረጋቸው ተነገረ።
በሀገሪቱ ቀደም ሲል የሽግግር መንግስቱን በተለይም ወታደራዊ ኃይሉን የሚያወግዙ ሰልፎች በሱዳን መዲና ካርቱም በተደጋጋሚ የተደረጉ ሲሆን፥ በቅርቡም ቅሬታ ባላቸው ወታደሮች የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም ተድርጎ ነበር፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ የሲቪል አስተዳደሩንና የለውጥ ኃይሉን የሚደግፉና የቀድሞውን የአልበሽርን መንግስት በመቃወም በሀገሪቱ የተካሄደውን ለውጥ ሲመራ የቆየው የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች ህብረት የተባለው የቅንጅት ኃይል አሁን ላይ የሱዳንን ወታደራዊ ቡድን የሚቃሙ ህዝባዊ ሰልፎችን እንደሚያስተባብር ተገልጿል፡፡
የሱዳን የሽግግር መንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በዋና ከተማዋ ካርቱም በየፊናቸው በመሰባሰብ በሱዳን አውራ ጎዳናዎች እና ከፕሬዚደንቱ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ድምጻቸውን ሲሰሙ ተደምጠዋል።
እነዚህ የፉክክር ሰልፎች በወታደራዊው ክንፍ እና በሲቪሉ የሽግግር መንግስት ቡድኖች መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ እንዲል ማድረጋቸዉን ነው አልጀዚራ በዘገባው የተነተነው።
በሲቪል አመራሩና በወታደራዊ ክንፉ የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት በ2023 ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ፥ ሱዳን የሽግግሩን መንግስት በሚቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል እና የሲቪል መሪዎች ሉዓላዊ ምክር ቤት እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሲቪል ካቢኔ እየተመራች ነው የምትገኘው፡፡
ሁለቱም ወገኖች ደጋፊዎቻቸውን ከማንኛውም ሁከት እንዲታቀቡ እና ተቃውሟቸዉን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የተቃውሞ ሰልፎቹ እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ሚዲያ ባደረጉት ንግግር፥ አገሪቱ ታይቶ በማታወቅ ቀውስ ውስጥ ናት ማለታቸው ይታወሳል።
በሚኪያስ አየለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.