Fana: At a Speed of Life!

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የማምረት አቅሙ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የማምረት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለና ምርቱን እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የማምረት አቅም ያለበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡
 
በጉብኝታቸውም ፋብሪካው የማምረት አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለና ምርቱን እየጨመረ እንደመጣ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
 
የሸገር ዳቦን የማምረት አቅም ከዚህ በላይ ለማሳደግ በከተማ አስተዳደሩ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች ካሉ በመወያየት ይፈታሉ ያሉት አቶ ጃንጥራር÷ፋብሪካው አሁን ባለው ቁመና የማምረት አቅሙን በመጨመር የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት መሙላት እንዳለበትም አሳስበዋል።
 
የሸገር ዳቦ ምርቱን ለመጨመር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው÷ በተሟላ ሁኔታ የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጎ በሙሉ አቅም ምርቱን በአጭር ጊዜ ማሳደግ እንዳለበት ከፋብሪካው አመራሮች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
 
በጉብኝቱም የአንድ ዳቦ የግራም ልኬት በምን አንደሚሰላ እና የግራም መቀነስ አለ ወይስ የለም የሚለውንም ለማየት ተሞክሯል ነው ያሉት፡፡
 
በዚህም ከተቀመጠው ስታንዳርድ አንፃር ምርቱ ጉድለት እንደሌለበት የፋብሪካው ስራስኪያጅ በዝርዝር አስረድተዋል።
 
ከሸገር ዳቦ በአሻገር ሁሉም የከተማዋ እንዱስትሪዎች የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርበት የሚያጋጥማቸውን ችግር ለምፍታት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
 
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው÷ የሸገር ዳቦ ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚ የሚደርስበትን አሰራር እና የቁጥጥር ሂደት ንግድ ቢሮው ዝርዝር አሰራር እንዳወረደ መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.