Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እንዲሁም አመጽና ግጭት ለመቀስቀስ በህቡዕ ሲሰራ የቆየ ቡድን ከእነ ግብረአበሮቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ – ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 21 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እንዲሁም አመጽና ግጭት ለመቀስቀስ በህቡዕ ሲሰራ የቆየ ቡድን ከእነ ግብረአበሮቹ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ÷ በቢሾፍቱና በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ከሚከበረው የኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶች ለመፈጸም፣ አመጽ ለማቀጣጠል፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ከጥቂት የህወሓት የጥፋት ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተልዕኮ ተቀብሎ በህቡዕ ሲያስተባብርና ሲመራ የነበረ የኦነግ ሸኔ ቡድን ከእነ ግብረአበሮቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረጉን አስታውቋል።

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን ባሰራጨው መረጃ እንደገለጸው ÷ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ፣ በቢሾፍቱና በሌሎቹም የአገሪቱ አካባቢዎች በጦር መሳሪያ የተደገፈ የሽብር ጥቃት፣ አመጽ ፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ተልዕኮ ለተሰጠው በህቡዕ የተደራጀ አንድ ታጣቂ ቡድን የሚውል 10 ክላሺንኮቭ የጦር መሳሪያ ከ 280 ጥይቶች ጋር ከመቀሌ ወደ ባቲ ሲጓዝ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም ቀን በደቡብ ወሎ ዞን ሃይቅ ከተማ ከእነ ተሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ውሏል።

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ህዝባዊ አመጽ እንዲነሳ በማድረግ ይህን እንቅስቃሴ ለማሳካት ከተመለመሉት መካከል አንዱ የሆነው እንድሪስ እያሱ መሃመድ የተባለ የኦነግ ሸኔ አባል ከትግራይ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊና ከሌሎች ጥቂት የህወሓት የጥፋት ቡድኖች ጋር በህቡዕ ተልዕኮውን ሲያቀናጁ እንደነበር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አመልክቷል።

እነዚህ የጥፋት ቡድኖች በመጪው ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልሎች የሚከበሩትን የኢሬቻ በዓልን ተገን በማድረግ በኦሮሚያ ክልል አመፅ እንዲቀጣጠልና ወደ ሌሎች ክአካባቢዎች እንዲዛመት በጦር መሳሪያ ጭምር የታገዘ ትርምስ ለመፍጠር ከመቀሌ ወደ መሃል አገር የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ሲልኩ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ለዚህ እኩይ ተግባራቸውም ግለሰቦችን መልምለው ወደ መቀሌ በመውሰድ አሰልጥነው ወደተለያዩ አካባቢዎች ይልኩ እንደነበር የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።

ለዚህ ተልዕኮው እንዲረዳቸው ካደራጇቸው የህቡዕ ቡድኖች መካካልም አንዱ እንድሪስ እያሱ መሃመድ በተባለ የኦነግ ሸኔ አባል የሚመራ ሲሆን ÷ ላለፉት ወራት ከከሚሴ፣ መቀሌ አዲስ አበባ በመመላለስ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

ቡድኑ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓመተ ምህረትም በደቡብ ወሎ ዞን ሃይቅ ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገልጿል።

የጥፋት ቡድን መሪው መቀሌ ከሚገኘው የትግራይ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ከሆነው ተኪኡ ምትኩና ሌሎች ጥቂት የህወሓት የጥፋት ቡድኖች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ወደ መቀሌ በመመላለስ የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብና ተልዕኮ በመቀበል ከሸኔ ታጣቂ ቡድን ጋር በማስተሳሰር በኦሮሚያ የአመጽ ቡድን ሲያደራጅ ቆይቷል።

ከዚህም በተጨማሪ እንድሪስ እያሱ መሃመድ እና ግብረአበሮቹ ከመቀሌ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት በባቲ የህቡዕ ቡድን አበላትን በማደራጀት በአካባቢው የብሄር ግጭቶችን የማስፋፋት እንዲሁም በሌሎችም ስፍራዎች ግጭት የመቀስቀስ ተልዕኮ ተቀብለው ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል።

አማርኛ፤ኦሮሞኛ፤ ሱማሊኛ፤ አፋርኛና አረብኛ በድምሩ አምስት ቋንቋዎችን የሚናገረው የሽብር ቡድኑ መሪና አስተባባሪ ተጠርጣሪው እንድሪስ እያሱ መሃመድና ግብረ አበሮቹን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በጥብቅ ሙያዊ ዲስፕሊን የመከታተልና መረጃ የመስጠት ስራዎችን ሲሰራ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የኢፌዴሪ መካላከያ ሰራዊት በጋራ መስራታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

መቀሌ ተሸርቦ ደቡብ ወሎ ዞን ሀይቅ ከተማ ላይ የከሸፈው የሽበር ጥቃት መሳሪያዎችን በከረዩና በባቲ በኩል ወደ ቢሾፍቱና አዲስ አበባ በማስገባት ከፍተኛ ሁከትና ግርግር በመፍጠር አገርን ለማተራመስ እቅድ እንደነበረው የጠቆመው መግለጫው÷ ሴራውን በማክሸፍ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉንም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ መግለፅ ይወዳል፡፡

በቀጣይም በአገራችንና በህዝባችን ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የሽብር ጥቃቶች አስቀድሞ በማወቅ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እያረጋገጠ የህብረተሰቡ ትብብርና ድጋፍም እንዳይለየውም ጥሪ አቅርቧል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.