Fana: At a Speed of Life!

የቅድመ ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሳይማሩ እንደማይመረቁ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2012 ቅድመ ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ሳይማሩ እንደማይመረቁ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ለሳይንስና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑና በስራ ላይ ያሉ 44 ዩኒቨርሲቲዎች ከመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የገጽ ለገጽ የመማር ማስተማር ሂደታቸውን ማቋረጣቸው ይታወሳል።

የሳይንስና ከፈተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፥ በቅድመ-ምረቃ መርሃ ግብር በቴክክኖሎጂ ትምህርት ማስቀጠል ባለመቻሉ ተማሪዎች ሳይማሩ አይመረቁም ብለዋል።

“በቴክኖሎጂ የቅድመ-ምረቃ ትምህርት ማስቀጠል ከሞላ ጎደል አልተቻለም፤ እያንዳንዱ ተማሪ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ የሚማረውን እያነበበ፤ ምዕራፍ በምዕራፍ፣ ሞጁል በሞጁል ተምሮ ምዘና እየተደረገለት አልቆየም።

በዚህ ረገድ ያልመጣን፣ የትምህርቱን ይዘት ያላጠናቀቀን ተማሪ ተምሯል ብሎ ወስዶ፤ ይህንን ኮርስ ጨርሰሃል፣ በዚህ መልኩ ተገምግመሃል እና ይህንን ውጤት አግኝተሃል ብሎ ውጤት ሰጥቶ ማስመረቅ በትምህርትም በአሰራርም ወንጀል ነው፤ መሰል አካሄድ አይፈቀድም፤ እንደዚህም አይሆንም!” ብለዋል።

የድህረ ምረቃ የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር በቴክኖሎጂ ማድረስ በመቻሉ ይመረቃሉ ከሚል ድምዳሜ ተደርሷል።

ሆኖም የቅድመ-ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ምረቃ በኮቪድ 19 የስርጭት መጠን የሚወሰን እንደሆነ ነው ዶክተር ሳሙኤል የተናገሩት፤ ይህም የምረቃ ዓመታቸውን ተገማች የማያደርገው ነው።

ሁሉም ሊባል በሚቻል ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው መሰረተ-ልማት ለቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች ትምህርትን በቴክኖሎጂ ማድረስ የማያስችል ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።

በ2012 የትምህርት ዘመን የቅድመ-ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውም ለዚሁ ነው፤ ተማሪዎቹን እንደማያስመርቁ ከወዲሁ ያስታወቁ አሉ።

ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ፈጽመው እንዳይርቁ በሚል በተለያዩ መንገዶች ትምህርት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ሲሰራ መቆየቱ የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በዳሶ፥ በሁሉም መርሃ ግብር ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች የመማር ማስተማር እያቀረበ ቢቆይም፣ በዚህ ዓመት ሊመረቁ የነበሩ የቅድመ-ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን እንደማያስመርቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲም የ2012 ቅድመ-ምረቃ የመደበኛ መርሃ ግብር ተማሪዎችን እንደማያስመርቅ ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ከቅድመ-መደበኛ የ2012 ዓም ተመራቂ ተማሪዎች የመደበኛ መርሃ-ግብር ተማሪዎች ብቻ የማይመረቁ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከውሳኔ ላይ አልደረሱም።

የገጽ ለገጽ ትምህርት ሲቋረጥ የሁኔታዎች ትንተና ሰርተናል ያሉት፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ፥ ተማሪዎቹ ወደ ግቢ ተመልሰው በአጭር ጊዜ መርሃ-ግብር የመጨረስ ዕቅድ ቢኖረንም የኮቪድ 19 ስርጭት ነባራዊ ሁኔታ ይወስነዋል ብለዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በቅድመ-ምረቃ የመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ ተማሪዎች ምረቃ ላይ ወጥ አቋም እያንጸባረቁ አይደለም። ሆኖም፤ የኮቪድ 19 ስርጭት የተገታ እንደሆነ ግን ተማሪዎችን በአፋጣኝ ወደ መደበኛ መማር ማስተማር ሂደታቸው የመመለስ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልፀዋል።

ተማሪዎች በሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም በየሚማሩባቸው ተቋማት የተዘጋጀላቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በማንበብ እየተዘጋጁ መጠበቅ አለባቸው የተባለውም ለዚሁ ነው።

በርስቴ ፀጋዬ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.