Fana: At a Speed of Life!

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭዎች ምዝገባ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመላ ሀገሪቱ ለአንድ አመት ያህል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ እና የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች ምዝገባ መጀመሩን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበጎ ፈቃዱ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉት እድሜያቸው ከ18 እስከ 35 የሆኑ ተመራቂዎች ሲሆኑ፥ ፍላጎቱ ያላቸው በጎ ፈቃደኞችም በየወረዳው በሚገኙ የፀጥታ ተቋማት መመዝገብ እንደሚችሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በሰላም ሚኒስቴር ድረ ገፅ ላይ ቀጥታ በመግባት መመዝገብ እንደሚችሉም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በዚህ በመጀመሪያው ዙር በብሄራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 10 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን እንደሚቀበልም፥ በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ አጋርነትና ተጠሪ ተቋማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ ለሶስት ወራት በአብሮ የመኖር እሴት፣ ተግባቦት፣ አቅም ግንባታ እንዲሁም የአካል ብቃት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማህበረሰቡን ለማገልገል ይሰማራሉም ነው ያሉት።

አገልግሎቱ ሀገርን ከማወቅና ህዝቦቿን ከማገልገል ባለፈ ጥሩ የስራ ልምድና የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ጠቅሰው፥ ለስራ እድል ፈጠራው የሰላም ሚኒስቴር ከባለስርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተመራቂ ወጣቶቹ በግብርና፣ ጤና፣ ግንባታ እና መሰል ዘርፎችን ጨምሮ ህብረተሰቡ አገልግሎት በሚፈልግባቸው መስኮች እንደሚሰማሩም ነው የተገለጸው።

በጎ ፈቃደኞቹ ስራ የሌላቸው በመሆኑም የምግብ፣ መኖሪያ እና ሌሎች መሰረታዊ ወጪዎችን መንግስት ይሸፍናል ያሉት ዳይሬክተሯ፥ የጤና እና የትራንስፖርት አገልግሎትንም የመንግስት ተቋማት በነፃ እንዲሰጧቸው ይመቻቻል ብለዋል።

ለአንድ አመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰጡት ወጣቶች 900 ሚሊየን ብር በጀት እንደሚመደብም አስረድተዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ ካደጉበት አካባቢ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሄደው አገልግሎት መስጠታቸው የኢትዮጵያን ባለ ብዙ ቀለም ባህል እና እሴት እንዲረዱ በማድረግና በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማገዝ አለኝታነታቸውን ለማሳየት እንደሚያግዛቸው ተገልጿል።

በጎ ፈቃደኞቹ የማህበረሰቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴት እና ስርአት እንዲጋሩ እና ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጥሩ የተለያዩ ፕሮግራሞች ይቀረፃሉ ተብሏል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.