Fana: At a Speed of Life!

የባህር ዳር ጢስ ዓባይ ፏፏቴ መንገድ በአስፓልት ደረጃ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪስት መዳረሻ ወደ ሆነው ጢስ ዓባይ ፏፏቴ የሚወስደው የባሕር ዳር ጢስ እሳት 22 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ እየተገነባ ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በፕሮጀክቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ የመስክ ሥራ ቅኝት አካሂዷል።

መንገዱ ከዚህ ቀደም በጠጠር ደረጃ የነበረ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ለብዙ ዓመታት ሲቸገሩ የቆዩ ሲሆን፥ አሁን ላይ ደረጃው ከጠጠር ወደ አስፓልት ኮንክሪት እንዲያድግ ተደርጎ ነው እየተገነባ የሚገኘው።

በአሁኑ ወቅትም የዲዛይን ቅየሳ፣ የአፈር ጠረጋ እና ድልደላ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ወደ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ የሚወስድ የ1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ለእግረኞች መጠቀሚያ ብቻ የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ግንባታ ሥራን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

ወደ ስፍራው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሃገር ጎብኚዎች የሚጓዙ በመሆኑ፥ ከዚህ ቀደም በመንገድ መሠረተ ልማት መጓደል ይፈጠር የነበረውን እንግልት ያስቀራል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ከ767 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን በሃገር በቀሉ ሚልኮን ኮንስትራክሽን እየተገነባ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.