Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የወረዳና የቀበሌ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2012(አዲስ አበባ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የምክር ቤት አባላት ቁጥር መወሰኛ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ መንግስት የአስፈፃሚ አካላት የ6 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለጉባኤው አባላት ቀርቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በሪፖርታቸው ባለፈው ግማሽ ዓመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች በተሰራው ስራ ተቀርፈው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን አመላክተዋል፡፡

ከአጎራባች ክልል ህዝቦች ጋር የነበረውን የቆየ ግንኙነት ለማጠናከር አልፎ አልፎ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በዕርቅና በይቅርታ በመፍታት አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መተከል ዞን አካባቢ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው መመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በእርሻ ዝግጅት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር እና አርሶ አደሩ እና ባለሃብቶች ወደ ስራ ባለመግባታቸው ምክንያት አፈፃፀሙ ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል።

በትምህርት ዘርፉም በክልሉ 312 ሺህ 396 ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ባሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡

መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ትግበራ ከተገባ በኋላም የእናቶችንና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራና መልካም ውጤት እየተመዘገበ መሆኑም ተመላክቷል።

በከተማና በገጠር ለ15 ሺህ 814 ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር መቻሉንም ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በክልሉ የተለያዩ ቀበሌወች ወረዳ እንዲሆኑ እና የስም ለውጥ በማድረግ እና በክልሉ 474 ቀበሌ የነበሩት አዳዲስ ቀበሌዎች ተጨምረው 518 ቀበሌ በመሆን እንዲጸድቅ መወሰኑ ተነግሯል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.