Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፅሐፍት ኤጀንሲ አቋርጦ የነበረውን አገልግሎት ታህሳስ 12 ቀን ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፅሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) በኮቪድ- 19 ምክንያት አቋርጦት የነበረውን አገልግሎት ከታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል መመሪያን ጠብቆ ቤተ መፅሐፍቱን ለህዝብ ክፍት ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን ያስታወቀው ኤጀንሲው ከታህሳስ 12 ቀን ጀምሮም የህጻናትና አካል ጉዳተኞች ቤተ መፅሐፍትን ሳይጨምር እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡

ወረርሽኙን ለመግታት እንዲያስችልም በፊት ያስተናግድ ከነበረው 1 ሺህ 200 ተገልጋይ በመቀነስ 326 ተገልጋዮችን ብቻ እንደሚያስተናግድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የመፅሐፍት ውሰት እንደማይኖርና አንድ ተገልጋይ የተጠቀመበትን መጽሃፍ ከተጠቀመ በኋላ ከሶስት እስከ አምስት ቀናት ተለይቶ እንደሚቀመጥም አስታውቋል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው አገልግሎቱ መመሪያ በማዘጋጀትና የመመሪያውን አተገባበር ለአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞቹ ስልጠና በመስጠት ፈትሿል፡፡

መመሪያው ከህብረተሰብ ጤና ኢኒስቱቲዩትና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከተቋሙ የስራ ባህሪ ጋር በማናበብ እና በማቀናጀት የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

መመሪያው ላይ የተቋሙ ሃላፊነት፣ የተገልጋይ ግዴታ፣ የጽዳት ክንዋኔንና ግንዛቤ የመፍጠር ስራን የተመለከቱ ሃሳቦች ተካተውበታል፡፡

በተቋሙ ድረ-ገጽ ላይም ለተገልጋይ አብራሪ በሆነ መልኩ ተደራሽ እንደሚደረግም ኤጀንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.