Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከሚሰነዝሩት እኩይ ተግባር የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ ፀረ-ሰላም ኃይሎች እየሰሩ ያሉትን አገር የማፍረስ ሴራ የማስቆም የመቆጣጠርና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታወቀ፡፡
 
የብሄራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴ ነገ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
 
በመግለጫውም በዓሉ በሰላም እንዳይከበር ለማድረግ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨትና በዜጎች ዘንድ መተማመን እንዳይኖር ውዥንብር ለመፍጠር አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ኮሚቴው አስታውቋል።
 
በተጨማሪም በበዓሉ ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ለማድረስ ሽብር ፈፃሚ ኃይሎችን በመመልመል፣ በማሰልጠን እና በማስታጠቅ እየሰሩ መሆኑን የጠቀሰው ኮሚቴው ለጥፋት የተሰማሩ ውስን ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የገለጸው።
 
የጥፋት ኃይሉ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የተለያዩ የሽብር ውዥብሮችን በመንዛት የለመደውን አገር የማፍረስ እኩይ ተግባሩን እንደቀጠለበትም ነው በመግለጫው የጠቀሰው።
 
በመሆኑም ይህ ውስን የጥፋት ኃይል በሀገሪቱ ለዘመናት የዳበረውን የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ለማፍረስ ሌት ተቀን እየሰራ በመሆኑ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ ብሄራዊ የፀጥታ አስተበባሪ ኃይሉ አስጠንቅቋል።
 
ህብረተሰቡም በሀገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን ሰላም ለማደፍረስ ውድመትና ሰቆቃ እንዲበዛ የሚታትረውን ኃይል እንደተለመደው ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ሰላሙን እንዲያስከብር ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
 
እንዲሁም በየደረጃው ያለው የጸጥታ ኃይል ፀረ-ሰላም ኃይሎች እየሰሩ ያሉትን አገር የማፍረስ ሴራ የማስቆም የመቆጣጠርና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑንም ነው በመግለጫው የጠቀሰው።
 
ኮሚቴው ማንኛውም ግለሰብ፤ ቡድን የአገሪቱን ህግ በማክበርና በማስከበር የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብሏል።
 
በተጨማሪም ህገወጥ እንቅሰቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ ህግን የተከተለ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ነው የገለጸው።
 
የብሄራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ኮሚቴው ነገ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የሰላምና የአብሮነት እንዲሆንም ምኞቱን ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.