Fana: At a Speed of Life!

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት በነገው ዕለት በጅግጅጋ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት በነገው ዕለት በጅግጅጋ እንደሚከበር ተገለጸ፡፡

ህዳር 29 የሚከበረው የብሄር ብሄረሰብ በዓልን አሰመልክቶ የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አሊ በደል መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ነገ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር በመግለፅ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት የተረጋገጠበት ቀን በመሆኑ በአሉ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት እና እኩልነት ቀን የሆነው የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 በየአመቱ እንደሚከበር በመግለፅ ዘንድሮ በሶማሌ ክልል ህዳር 17 ቀን 2013 ከተለያዩ ክልል የተውጣጡ ባለስልጣናት እና የብሄር ብሄረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ይከበራል፡፡

አቶ አሊ ህብረተሰቡ በአሉን ለማክበር ወደ ሶማሌ ክልል የሚመጡ የክብር እንግዶቹንና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን በአክብሮት ፣ አንድነት እና አብሮ መኖር እሴትን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲቀበልም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

ሀላፊው ሰሞኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህወሃት የጥፋት ቡድን ላይ እየወሰደ የሚገኘውን ህግን የማስከበር እርምጃ የክልሉ ህዝብና መንግሰት እንደሚደግፉ ተናግረዋል ፡፡

ህወሀት በስልጣን ዘመኑ ከሰዉ ልጅ የማይጠበቅ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊቶችን በሶማሌ ህዝብ ላይ ሲፈፅም እንደነበር በመግለፅ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገር አንድነት መርሆዎችን እና የህዝቦችን ጥቅም እንዲያከብሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የጋራ አንድነትና የህዝብን ጥቅም በጋራ ለመቆም የተቃዋሚም ሆነ የገዥ ፓርቲ ሃላፊነት ነው ብለዋል ፡፡

እንደ መንግስት በሀሰተኛ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩ አካላት በህግ እንደሚጠየቁና ህጉም ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ማለታቸውን ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገነነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.