Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር ስልጠና በአዳማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር ስልጠና በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ መካሄድ የጀመረው ስልጠና እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚቀጥል የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ መለስ አለሙ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በመክፈቻው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተዋል።

ስልጠናው ፓርቲው ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና ሃገራዊ ውህድ ፓርቲ ከተሸጋገረ በኋላ በየደረጃው ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ምንነትና አስተሳሰብ ዙሪያ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በተጀመረው ሃገራዊ ለውጥና ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በተገኙ ስኬቶችና የቀጣይ ስጋቶች ላይ አመራሩ የተግባር አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑንም አቶ መለስ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ለሃገሪቱ ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባትና ለቀጣይ ተልዕኮ ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ ነውም ብለዋል።

ይህንኑ አላማ ለማሳካት በመድረኩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳልም ነው ያሉት።

በሃገሪቱ የተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ ምንነቱን፣ ባህሪውንና የተገኙ ስኬቶችን በአግባቡ በመገንዘብና በማስፋፋት እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት የውይይቱ አጀንዳ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

ውይይቱ በተለይም የህዝቡን የህግ የበላይነት፣ የማህበራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም በቀጣይ የጋራ አቅጣጫዎች ላይ ለመግባባት የሚያስችል የሃሳብ ልውውጥ እንደሚካሄድበትም ጠቅሰዋል።

በስልጠናው ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልፅግና እስከ ፖለቲካዊ ብልፅግና ያሉ የርዕዮተ አለም አስተሳሰቦችና እሳቤዎች ላይ አመራሩ በጥልቀት ይመክራል ነው የተባለው።

ለ17 ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ አመራሮች ይሳተፋሉ።

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.