Fana: At a Speed of Life!

የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ትብብርና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠል የሀገሪቱ ፓርላማ ጥምረት ቡድን በመንግስታቸው ላይ ግፊት እንዲያድርጉ ተጠየቀ፡፡
በብሪታኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ÷ በፓርላማ ተገኝተው ለብሪታኒያ ፓርላማ ጥምረት ቡድን አባላት የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የልማት ድጋፍ ወደቀደመው መጠኑ እንዲመለስ የፓርላማ አባላቱ በመንግስታቸው ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ከአውሮፓ መውጣቱን ተከትሎ በካሄደው የውጪና የመከላከያ ፖሊሲ ክለሳ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው አገራት ዋነኛዋ እንደነበረች ያስታወሱት አምባሳደር ተፈሪ÷ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱም በተገባው ቃል መሰረት እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ኢትዮጵያ በፖሊሲና በእቅድ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ቀርጻ ከራሷ በማለፍ ለጎረቤት ሀገሮች እና ለአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ያደጉ ሀገሮች የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የገቡትን 100 ቢሊየን ዶላር በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚደረግ ድጋፍ በተገባው ቃል መሰረት እንዲፈጸም የብሪታኒያ መንግስት የጀመረውን ግፊት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በማስመልከትም አምባሳደር ተፈሪ ሀገሪቷ ሰላምን በተመለከተ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ለብሪታኒያ ፓርላማ አባላት አስረድተዋል።
የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየወሰደች ያለውን እርምጃ አድንቀው፥ ያደጉ ሀገሮች የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ በብሪታኒያ መንግስት በኩል ግፊቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍ ከኮቪድ ተጽዕኖ እና በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት እንደቀነሰ እንደሚረዱ ያመለከቱት የፓርላማ አባላቱ÷ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በመጠየቅ ለመንግስታቸው እንደሚያቀርቡ ማስረዳታቸውን በለንደን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ የልማት ድጋፍና ትብብሩ በትምህርት፣ በጤና፣ በእናቶችና ሕጻናት እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች መሆኑን አስታውሰው፥ በርካታ ውጤታማ ተግባሮች መከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የድጋፍ መጠኑ በመቀነሱ በእቅድ የተያዙ የማህበራዊ አገልግሎቶች አፈጻጸምን እንዳጓተተ ነው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.