Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከህወሓት ጋር በመቀናጀት በሀሰት ዜና አለም አቀፉን ማህበረሰብ እያሳሳቱ ነው -መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በመቀናጀት በሀሰት ዜናዎች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያሳሳቱ መሆኑን መንግስት ገለፀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ መገናኛ ብዙሃኑ ከሽብር ቡድኑ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ በማሳሳት ስራቸው ረጅም ርቀት ተጉዘዋል ነው ያለው፡፡

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህወሓት አሸባሪ ቡድን ግጭት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ አሸባሪ ቡድኑ ÷ መንግስት ላይ የሃሰት ውንጀላዎችን ሲያቀርብ ነበር ያለው መግለጫው የሃሰት ውንጀላውም መሬት ላይ ከሚታየው እውነታ ጋር ፍጹም የተቃረነ ነው ብሏል፡፡ እውነታውንም ለመመልከት የሚፈልግ ማንኛውም ዓለም አቀፍ አካል በቦታው ተገኝቶ ማረጋገጥ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው ÷ ምንም እንኳን አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ጸብ አጫሪነት ፣ መንገድ በመዝጋቱ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ድጋፍ ቢቋረጥም መንግስት ግን እርዳታው ለትግራይ ህዝብ እንዳይደርስ የማሰናከል ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለው እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚያልፍበት ኮሪደርም ክፍት እንደሆነ ነው ያስታወቀው።

የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ መኪኖችም ከጅቡቲ ወደብ ተነስተው በአፋር በኩል አድርገው ወደ ትግራይ እንደሚሄዱ ነው በመግለጫው ያመላከተው፡፡

ነገር ግን አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ ግጭቱን ወደ አፋር አካባቢዎች በማስፋት አቅርቦቱን ለማስተጓጎል ሙከራ አድርጎ እንደነበርም በመግለጫው አመላክቷል።

ምንም እንኳን ሃቁ ይህ ቢሆንም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እውነታውን እያወቁ በመካድ እውነቱን ከመዘገብ ተቆጥበዋል ሲል አስምሮበታል፡፡

መንግስት በአሸባሪው ቡድን ለደህንነት ስጋት ሊሆን ከሚችል ማንኛውም ነገር ራሱን ለመከላከልም ለተወሰነ ጊዜ ወደ ትግራይ የሚደረግ የአየር በረራ አቋርጦ ነበር ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአየር በረራ እንደተጀመረና ተቋርጦ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትም ወደ ትግራይ የማድረስ ስራ አሁን ላይ የአልሚ ምግብና የመድሃኒት አቅርቦት በማመላለስ ተጀምሯል ነው ያለው በመግለጫው፡፡

ቢሆንም ግን አሁንም አሸባሪው ቡድን ዓለም አቀፋዊ ሃዘኔታን ለማግኘት የሃሰት ወሬውን መንዛት ቀጥሏል ሲል መግለጫው ያነሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሲ ኤን ኤን የተሰኘው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በትግራይ የዘር ማጥፋት መፈጸሙን የሚገልጽ የሃሰት ዘገባ ለመስራት መሰናዳቱን ከታማኝ ምንጮች ደርሶታል ሲልም ገልጿል።

አሸባሪ ቡድኑ ያልተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን በትግራይ ህዝብ ላይ እንደተፈጸሙ አድርጎ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች አስቀድሞ በመልቀቅ፥ ራሱ ህወሓት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ አባላት ላይ ፈጽሞት “ድንገተኛ መብረቃዊ ጥቃት” ብሎ የሰየመውን ጭፍጨፋ ለመሸፈን ጥሯልም ነው ያለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው፡፡

በተቃራኒው የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ጉዳት እንዳይደርስበት ለመታደግ መከላከያ የያዛቸውን አካባቢዎች ጭምር እየለቀቀ እንዲወጣ በማድረግ ከፍተኛ የነፍሥ ማዳን ጥረት አድርጓል ነው ያለው፡፡

ከፈረንጆቹ ሰኔ 2021 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የመከላከያ ሠራዊት ጦር ውጊያ በክልሉ እንዳላደረገ ነው ያስታወቀው፡፡

ይልቁንም በተቃራኒው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጦሩን በሰው ማዕበል በማጀብ የአፋርን እና አማራ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟልም ብሏል መንግስት ኮሙኒኬሽን ፡፡

ይህም ትግራይ ላይ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ የት የተካሄደ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል ሲልም ይጠይቃል፡፡

የዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃንም የተቀነባበረ ሴራ የሚጀምረው አሸባሪው ቡድን የጨፈጨፋቸውን ንጹሃን በመንግስት እንደተጨፈጨፉ አድርገው ማቅረብ ከመጀመራቸው ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 8 ቀን 2021 ሲ ኤን ኤን “ሰዎች ከእስር ካምፖች እየወጡ ነው፤ ከዛም አስከሬኖች ወንዝ ላይ ተንሳፈው ታዩ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ሰዎች ላይ ግድያ እንደተፈጸመ እና ወደ ወንዝ እንደተጣሉ በመግለጽ የሃሰት መረጃ አሰራጭቷል ብሏል የመንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው ፡፡

በዘገባው ጭፍጨፋው የተፈጸመው በሁመራ እንደሆነና የመንግስት የጸጥታ አካላትም ወንጀሉን እንደፈጸሙ ተደርጎ ቀርቧልም ነው ያለው መግለጫው፡፡

ዜናው የተቀነባበረና ለምዕራቡ ዓለም አሳማኝ በሆነ የታሪክ አወቃቀር የቀረበ በመሆኑ በእጅጉ እውነት የሚመስል አሳሳች መረጃ ቀርቧል፤ አማካዩን የምዕራብ ዓለም የማኅበረሰብ ክፍልም አሳስቷል ነው ያለው መንግስት።

በዘገባዎቹም በታቀደበት መልኩ “ደሃ አፍሪካዊት አገር እና ህዝቦቿን የሚጨፈጭፍ አምባገነን መንግስት” በማኅበረሰቡ ለመሳል ተሞክሯል ብሏል የመንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ይህን የተቀነባበረ የመገናኛ ብዙኃን ሤራ ለመስራት ያሰበው ሳማንታ ፓወር ከሀምሌ እስከ ነሃሴ ወር ባሉት ቀናት ውስጥ ሱዳንን ለመጎብኘት ማቀዳቸውን ተከትሎ ትኩረት ለመሳብ በማቀድ ነው ሲልም ያነሳል፡፡

መንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው አንዱ ዜና የተሰራው በሬውተርስ ሲሆን 30 አስከሬኖች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እና በሱዳን መካከል በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ተጥለው ሲንሳፈፉ እንደተገኙ አድርጎ መዘገቡን አስታውሷል።

አሶሺየትድ ፕሬስም ተመሳሳይነት ያለው ዘገባ ርዕስ በመቀየር ሰርቷል ነው ያለው መግለጫው፡፡

በርካታ የዜና ማሰራጫ መገናኛ ብዙኃንም በተቀናጀ መልኩ እና እውነታውን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ፍላጎት ሳያሳዩ የሃሰት ፕሮፖጋንዳውን በዘመቻ ሲያካሂዱ ተስተውለዋል ሲል ገልጿል፡፡

እንደዚህ ያለ የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርን ያልጠበቀ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በአፍሪካ አገራት በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና ባሕል እየሆነ መጥቷል ነው ያለው፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በተቀናጀ መልኩ በፕሮፖጋንዳቸው የዓለምን ህዝብ በማሳሳታቸው ቢገፉበትም፥ ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግስት በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን በመግዛት ለመለወጥ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ነው ያለው መንግስት በመግለጫው።

ህዝቡም መረጃው የተሳሳተ መሆኑን በመረዳቱ እና አላማቸውን በማወቁ በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል ሲልም ያስታውሳል።

መንግስት ኮሙኒኬሽን በመግለጫው አሁንም እነዚህ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስህተታቸው ባለመማር የሃሰት ፕሮፖጋንዳቸውን ማሰራጨት መቀጠላቸውን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም መገናኛ ብዙኅኑ በድጋሚ የሚያሰራጩት የሃሰት መረጃ ሚሊየኖችን እየጎዳ መሆኑን አውቀው ከእንዲህ አይነት ተግባራቸው እንዲታቀቡ ጥሪውን ያቀርባል ሲል መንግስት ኮሙኒኬሽን አሳስቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.