Fana: At a Speed of Life!

የቱርክ ባለሃብቶች በአፋር ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርክ ባለሃብቶች በአፋር ክልል የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ።
በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰመራ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት ፥ ቱርክና ኢትዮጵያ የቆየ ወዳጅነት ያላቸዉ ሀገሮች ናቸዉ።
እንዲሁም ቱርክ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት አጀንዳዎችና ኢንቨስትመንት ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
የቱርክ አምባሳደሮች በተለያዩ ጊዜያት በአፋር ጉብኝት ማድረጋቸዉን አስታውሰው ፥ ከዚህ በፊት በክልሉ በነበረዉ ድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ የሁለቱን ሃገራት ወዳጅነት በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
የአምባሳደሯ ጉብኝትም ይህን ወዳጅነት የሚያስቀጥል መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፥ ቱርካዉያን ባለሃብቶችም በክልሉ በጨዉ አይወዳይዜሺን እየተሳተፉ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪም በሪል እስቴትና ኬሚካል ኢንዱስትሪ መስክም ለመሰማራት ቦታ የወሰዱ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ በማዕድንና በግብርና መስክ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ያለዉ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ በዘርፎቹ ለሚሠማሩ ቱርካዉያን ባለሃብቶች ክልሉ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደር ያፕራክ አልፕ እና ልዑካቸው ከሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሀመድ ዑስማን እና ሌሎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በውይይታቸው ሠመራ ዩኒቨርሲቲ ከተግባር ተኮር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚመደብ እንደሆነና የልህቀት ትኩረቱም በማዕድን፣ ግብርና እና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ እንደሆነ ተብራርቶላቸዋል።
አምባሳደር አልፕ ቱርክ በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን የካበተ ልምድ ለማካፈልና አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ በርካታ እድሎች እንዳሉ አብራርተዋል።
በዋናነት የትምህር ዘርፉን ለመደገፍና የትምህርት እድልን ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነትም የኤምባሲው የትምህርት ተወካይ ሌቬንት ሳሂን እና የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተፈራርመዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.