Fana: At a Speed of Life!

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለአፍሪካ ልዩና ሞዴል ፕሮጀክት ነው – ኢ/ር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ልዩና ለአፍሪካውያን ሞዴል ፕሮጀክት መሆኑን የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡
ሁለተኛው የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፀጥታው ምክር ቤት የሕዳሴው ግድብ ድርድር ጉዳይ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት ሚኒስትሩ፣ አምባሳደሮችና የተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ላደረጉት ጥረት የግሉ ዘርፍ የውኃ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ባዘጋጁት የውይይትና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለማልማትና ሀገራቸውን ለማበልጸግ ከግላቸው ገንዘብ በማሰባሰብ የሚገነቡት በመሆኑ በዓለም ላይ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሞዴል እንደሆነና ሕዝቦች በራሳቸው አቅም መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወንና ሀገራቸውን ማበልፀግ እንደሚችሉ ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በፀጥታው ምክር ቤት የተገኘው ውጤትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ፣ የዲፕሎማቶችና የበርካታ ምህሩን ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የሚደረገው ድርድር ገና ያልተጠናቀቀና በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚቀጥል መሆኑን ያወሱት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በመርሆዎች ስምምነት መሠረት ቀናነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ድርድሩን እንደምትቀጥል መናገራቸውን ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.