Fana: At a Speed of Life!

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ህዝቡን ለተሻለ ተሳትፎ ማነሳሳቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መከናወን ህዝቡን ለተሻለ ተሳትፎ ማነሳሳቱን የኦሮሚያ እና የአማራ የክልል የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ገለጹ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አመራሮች ÷ከግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት በኋላ የህዝቡ የቦንድ ግዚ እና የ8100 ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል የህዳሴ ግድቡ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ካሳሁን ታዬ÷ በተጠናቀቀው የበጀት አመት ክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት ተከትሎ የተፈጠረውን ህዝባዊ መነሳሳት ወደ ድጋፍ ለመቀየር ክልሉ እየሰራ መሆኑንም ሃላፊው ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ተናኜ አበበ በበኩላቸው÷ በዘንድሮ አመት ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ግዢ በህዝብ ተሳትፎ መመዝገቡን ተናግረዋል።

ሃላፊው አያይዘውም በመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ደስታ ብርታት የሆናቸው የክልሉ ወጣቶችም እስከ መስከረም መጨረሻ 500 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅደዋል ነው ያሉት ።

ከዚያም ባለፈ ባለፉት ሳምንታት በተደረገ የቦንድ ግዢ ዘመቻዎች እስከ 3 ሚሊየን ብር ገቢ መደረግ ተችሏል ብለዋል ።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ህዝቡን ለተሻለ ተሳትፎ አነሳስቶታል ያሉት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል የህዝባዊ ተሳትፎ ጽህፈት ቤቶች ፣ህዝቡ አሁንም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል ።

በሀይለየሱስ መኮንን

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.