Fana: At a Speed of Life!

የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሠላማዊ ዜጎች ሊጠቁ አይችሉም – ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ ጥር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ አየር ኃይላችን የታጠቀው መሳሪያና ቴክኖሎጂ ዒላማውን ለይቶ የሚመታ በመሆኑ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡
አሸባሪው ህወሃት “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” ሲል የሚያቀርበውን ውንጀላ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአየር ኃይሉን ዝግጁነትና ብቃት የሚያጎለብቱ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በብቃት በመመከት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና በመጫወት አገርን ከመፍረስ ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጥቃት ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተደራጀ ነው ያሉት ዋና አዛዡ፥ “የታጠቅነው ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ የተሰጠውን ዒላማ በብቃት የሚመታ በመሆኑ በምንም መልኩ ሠላማዊ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ አይችሉም” ብለዋል።
ከዚህ አኳያ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል “በትግራይ ክልል በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው” በሚል የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አየር ኃይሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለውና በጠንካራ ሥነ ምግባር የተገነባ በመሆኑ የትኛውም ዓይነት ኦፕሬሽኖች ሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
የአየር ኃይሉ ዘመናዊ ትጥቆች ማንን እና ምን መምታት እንዳለብን በዓይናችን አይተን እንድንወስን የሚያደርጉ በመሆናቸው በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈጸም አይችልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ህፃናትን የያዙ እናቶችን ጭምር አስገድዶ በጦር ካምፕ ውስጥ በማስገባት የጥቃት ዒላማ እንደሆኑ አስመስሎ ፊልም በመቅረጽ እንደሚያሰራጭ ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችም የራሳቸው የሆነ መለዮ የሌላቸው በመሆኑ የቡድኑ አመራሮች በጦርነቱ የሞቱባቸውን ታጣቂዎች አስከሬን በመሰብሰብ ሠላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ አስመስለው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየጣሩ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
የአየር ኃይሉ ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን በሚመጥንና ኢትዮጵያውያንን በሚመስል መልኩ የተገነባ እንዳልነበር ጠቅሰው፥ በአንድ አካባቢ ሰዎች ታጥሮ ለአንድ ፓርቲ ህልውና ሲሰራ እንደቆየም አንስተዋል።
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ለታላቅ አገር የሚመጥንና የሁሉም ኢትዮጵያውያን የሆነ ተቋም መገንባት መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ይህን ተከትሎ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ወጣቶች ተቋሙን በመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተናግረዋል፡፡
አየር ኃይሉ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከደህንነት ስጋት ነፃ እንዲሆን በመጠበቅ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያለምንም ችግር የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
ተቋሙን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ይበልጥ ለማዘመን አዳዲስ አሰራሮች ወደ ትግበራ እንደሚገቡም አስታውቀዋል፡፡
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.