Fana: At a Speed of Life!

የትራምፕ ንግግር በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው – በሩሲያና ቤላሩስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሩሲያና ቤላሩስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትራምፕ ንግግር በኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት መሆኑን ገለፁ።

በሩሲያ ፌዴሬሽንና በቤላሩስ ሪፐብሊክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግርን አስመልክቶ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብፅ ጥቃት መሰንዘር እንደምትችል ያነሱት ሀሳብ ከአንድ የታላቅ ሀገር መሪ የማይጠበቅ፣ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የዘመናት ግንኙነት ያላገናዘበ በምስራቅ አፍሪካ ታላቅ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን ታሪክ ጠንቅቆ ካለመረዳት የመነጨ፣ በታሪክ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሆኑ ህዝቡ ለውጭ ሀገር እርዳታ ብሔራዊ ጥቅሙን አሳልፎ የማይሰጥ መሆኑን ያላገናዘበ እንደሆነም አንስተዋል።

በአቋም መግለጫቸው የዶናልድ ትራምፕ ንግግር በኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ የጥቃት ጥሪ በመሆኑ አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።

“ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል የተጀመረው ድርድር የሁሉንም ሀገሮች ጥቅም በጠበቀ መንገድ እንዲቋጭ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በህልውናው ላይ የተቃጣውን ጥቃት ከመንግስት ጎን በመሆን ለውጭ ጠላት አይበገሬነቱን ለማሳየት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአንድነት መንፈስ እንዲነሳም ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ለማስከበር እንዲሁም የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ያለንን ዝግጁነት እንገልጻለን ብለዋል በመግለጫው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.