Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ግንቦት 20ን በማስመልከት ያወጣው መግለጫ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ግንቦት 20ን በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግንቦት 20ን ሲያከብሩ የቆዩት የአርነት ችቦ አውለብልበው የስልጣን ባለቤት በመሆናቸው ነው ብሏል።

ግንቦት ሃያን የሚያከብሩትና በጉጉት የሚጠባበቁት የህዳሴ ጉዞ ያወጁበት ቀን በመሆኑ እንደሆነ በመጥቀስም፥ ኢትዮጵያን በ2017 ዓመተ ምህረት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ ግልፅ ራዕይ ተቀምጦ፣ በሃገራችን ሰላም እንዲነግስ፣ ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ እና ዙሪያ መለስ ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ፥ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መሰረታዊ እምነቶችና ምሶሶዎችን መነሻ ያደረጉ ዓበይት ግቦችን ለማሳካት ወደር የለሽ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋልም ብሏል።

ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው የቀድሞው ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት አረጋግጧልም ነው ያለው፤ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትም የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ክብር ከፍ የሚያደርግ ተግባር መፈጸሙን በመጥቀስ።

ይሁንና በህዝቡ ጠያቂ ፍላጎት ማደግና በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር መንሰራፋት ምክንያት ይህ የሚያስጎመጅ ግስጋሴና ዕድገት መቀጠል አልቻለም ነው ያለው።

ከህወሓት በስተቀር የቀድሞዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ባለማካሄዳቸው ችግሩ ሊፈታ አልቻለም ብሏል የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ።

አያይዞም “አሁን ያለው የፌደራል ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው አካል” ይላል መግለጫው፥ “ዜጎችን ለመፈናቀልና በፖለቲካዊ እምነታቸውና በማንነታቸው ብቻ በየእስር ቤቱ እንዲታጎሩ አድርጓል” ይላል።

የፌደራል መንግስቱ ላይ ጠንካራ ወቀሳ የሚሰነዝረው መግለጫው “የፌደራል መንግስቱ የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት በሚያዋርድ መልኩ የሀገሪቱን የፖሊሲ ነጻነት አሽቀንጥሮ በመጣል ሁሉንም መግቢያ በሮች ለውጭ ሀይሎች ከፍቷል” በማለት ይከሳል።

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመግለጫው ለትግራይ ክልል ህዝብ ባስተላለፈው መልዕክት “ኮሮና ቫይረስንና የበረሃ አንበጣን በመመከት ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ በግንቦት 20 የተጎናጸፍካቸውን ዘርፈ ብዙ ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ተረባረብ” ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መሪዎችና ምሁራን ባስተላለፈው ጥሪም “ኮሮና ቫይረስን በጋራ እየመከትን 6ኛውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በጋራ እንድንንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.