Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ቡድን በአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ መንደር የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ቡድን በአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ መንደር የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር አክሊሉ ሀይለሚካኤል በኢንቨስትመንት ቡድኑ ፕሬዚዳንት ሰሂቼንግ ዣንግ ከተመራው ልኡክ ጋር በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች እና በኢንቨስትመንት ቡድኑ ፍላጎት ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዶክተር አክሊሉ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ትልቅ እና ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤታማ የቻይናውያን ኢንቨስትመንቶች እንዳሉ ጠቅሰው፥ የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ቡድን በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ መንገደር ለመገንባት ያሳየውን ፍላጎትም አድንቀዋል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ የያዘውን የኢንቨስትመንት እቅድ እንዲያሳካም መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ቡድን ፕሬዚዳንት ሰሂቼንግ ዣንግ በበኩላቸው፥ ኩባንያው በአዲስ አበባ ባለብዙ ዘርፍ የኢንዱስትሪ መንደር የመገንባት እቅድ እንዳለው ገልፀዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ የመንደሩ የኤሌክትሮኒክስ ማምረቻ እና የሶፍትዌር ማበልፀጊያ ማእከላትን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሎ ሆቴሎችና አፓርትመንቶችንም በውስጡ የያዘ ነው።

የኢንቨስትመንት ቡድኑ በኢትዮጵያ የያዘውን እቅድ እንዲያሳካ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላቸው እምነታቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

ከኢንዱስትሪ መንደሩ በተጨማሪም የቻይና ዩናይትድ ኢንቨስትመንት ቡድን የኢትዮጵያን ጥሬ እቃ እንጨት ተጠቅሞ የተለያዩ የቤትና የቢሮ መገልገያዎችን ማምረት፣ የፈርኒቸር እና የቦርድ ማመረቻ የመክፈት ፍላጎት እንዳለውም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.