Fana: At a Speed of Life!

የቻድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጸመባቸው ጥቃት የተገደሉት የቻድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

በዋና ከተማዋ በተካሄደው የቀብር ስነ ስርዓት ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሟቹ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።

በወታደራዊ ምክር ቤት ለሚመራው የሽግግር መንግስት ድጋፏን የገለፀችው ፈረንሳይ በፕሬዚዳንት ማክሮን በኩል የቻድን ደህንነነት እና ግዛታዊ አንድነት እንደምትደግፍ ገልፃለች።

ነገር ግን ወታደራዊ ቡድኑ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስተላልፍ አሳስበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከአማጽያን ጋር ውጊያ ላይ ያሉትን ወታደሮች ለመጎብኘት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጉብኝት ላይ በነበሩበት ወቅት ጉዳት ከደረሰቸው በኋላ ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በሀገሪቱ ለስድስተኛ ጊዜ የተካሄደውን ምርጫ 80 በመቶው ድምጽ አግኝትው የነበሩትን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት በመተካት ልጃቸው ማሃመት ኢድሪስ ዴቢ የሚመሩት ወታደራዊ ምክር ቤት ስልጣኑን መረከቡ ይታወሳል።

ባለ አራት ኮኮቡ ጄኔራል የ37 ዓመቱ ልጃቸው ማሃመት ኢድሪስ ዴቢ የሚመሩት ወታደራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱን ተክቷል ሲል የሀገሪቱ ጦር አስታውቋል።

በቻድ ህገ መንግስት መሰረት በፕሬዚዳንቱ ላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር ለ40 የሽግግር ቀናት ወይም እስከ ምርጫ ወቅት ሀገሪቱን የሚመራው የህግ አውጪ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንጂ ወታደራዊ ምክር ቤት አልነበረም ተብሏል።

ነገር ግን የተቋቋመው የሀገሪቱ ጦር ምክር ቤት ህግ አውጪው ሲበትን ፤ የሀገሪቱን ህገ መንግስት ማጠፉን ይፋ አድርጓል።

ይህም ወታደራዊ ምክር ቤቱ የራሱን ህገ መንግስት የመተካት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ያመለክታል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንቱ በ1990ዎቹ በሀገሪቱ የተነሳውን አመጽ ተከትሎ ነበር ወደ ስልጣን የመጡት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.