Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ባለስልጣኑ አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን አስጠነቀቀ፡፡
በቀን ከዘጠኝ ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ቢሆንም ተጠቃሚው ዘንድ በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑንም ነው ባለስጣኑ የገለጸው፡፡
የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን የነዳጅ ስታንዳርድ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ÷ ነዳጅ የጫኑ የአቅራቢ ድርጅቶች ቦቴ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የመዘግየት ችግር መኖሩን ጠቁመው÷ ነዳጅ የጫኑት ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የሚዘገዩበት ምክንያትም ዋጋ ከዛሬ ነገ ይጨምራል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አዲስ ዋጋ ሲታወጅ በሚኖረው ልዩነት ለማትረፍ በመፈለግ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደዚህ ዓይነት ችግር ከመፍጠር በማይቆጠቡ የነዳጅ አቅራቢዎች ላይ ማደያን ከማሸግ ንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አቶ ለሜሳ አስጠንቅቀዋል።
ነዳጁ በወቅቱ ተጠቃሚ ዘንድ እንዲደርስ ለማስቻል ከመነሻ እስከ መድረሻ ባለው የማጓጓዝ ሂደት÷ ከየክልሎች የንግድ ቢሮዎች ጋር በመተባበር የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ለኢቢሲ የገለጹት፡፡
አራት እና አምስት ማደያ ያላቸው ኩባንያዎች በአንዱ ብቻ አገልግሎት እያቀረቡ ሌላኛው ላይ አገልግሎት ያለመስጠት ክፍተት ይስተዋላል ያሉት ኃላፊው÷ ይህም የትራንስፖርት አገልግሎቱ ቀልጣፋ እንዳይሆን ማነቆ ሆኗል ብለዋል፡፡
በአፋር ክልል ነዳጅ ጭነው ተደብቀው የነበሩ 15 ቦቴዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወሱት የጠቀሱት አቶ ለሜሳ÷ ክልሉ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።
ነዳጅ በማጓጓዙ ሂደት ከአዋሽ ጀምሮ ያለውን የተሽከርካሪ መዘግየት ለማስቀረት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ተመድበው ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 200 ማደያዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ የነዳጅ ስርጭቱ ፍትሐዊ እንዲሆን በየአካባቢው ያሉ የንግድ ቢሮዎች ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሽከርካሪዎችን መመለከት የተለመደ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን ለማስተካከል የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ በየከተማው ያሉ የንግድ ቢሮዎች ቁጥጥራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.