Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ጥቅል ኢኮኖሚው ላይ መስራት እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሸቀጦች የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ጥቅል ኢኮኖሚው ላይ መጠነ ሰፊ ስራዎችን መሰራት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ።

የአገልግሎትም ሆነ የቁሳቁስ የመሸጫ ዋጋ በተከታታይ ሲጨምር የዋጋ ንረት ተከስቷል ማለት እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ምሁራኑ አቶ ዋሲሁን በላይ እና ዶክተር ንጉሴ ስሜ፥ ለኑሮ ውድነቱ እያደገ ያለው የተጠቃሚው የመሸመት ፍላጎት እና የገበያ አቅርቦት አለመመጣጠን ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

በገበያው ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን ማደግ እና በዚሁ ልክ የምርት መጠን አለማደጉ ለግሽበቱ ምክንያት እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

ከዚህ ባለፈም በሃገሪቱ በቅርብ ጊዜያት የተስተዋሉ እና እየተስተዋሉ የሚገኙ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች በዋጋ ንረቱ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውንም ገልጸዋል።

መንግስት የወጪ ንግድን ለማበረታታት በሚል የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ በውጭ ብድር የሚሰሩ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ አለመቻላቸው በዋጋ ንረቱ ላይ አስተዋጽኦ አለውም ነው የሚሉት።

የዋጋ ንረቱም በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ከ20 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፥ በዚህ አመት የተወሰኑ ወራት ያሳየው እድገት ባለፉት አምስት አመታት ታይቶ የማይታወቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ፍላጎት ተኮር የሆነውን የምጣኔ ሃብት ጉዞ ከአቅርቦት ጋር የተመጣጠነ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ግብርናን እውን ማድረግ፣ የመስኖ ልማቶችን በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ለማምረቻው ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባልም ነው የሚሉት።

ከዚህ በተጨማሪም ለዋጋ ግሽበቱ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያለውን የሃገሪቱን የገበያ ስርአት መቃኘት፣ የግል ባለሃብቱን ከአገልግሎት ዘርፉ ባሻገር በኢንቨስትመንት ላይ ተሳታፊ ማድረግ እና ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ ላይ ትኩረት በመስጠት የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በአወል አበራ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.