Fana: At a Speed of Life!

የኒኩሊየር ኃይልን ለሠላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ህዳር 18፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ሀይል ኤጀንሲ የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር ዶ/ር ሻውካት አብዱልረዛቅ ጋር የኒኩሊየር ኃይልን ለሠላማዊ ዓላማ ለማዋል በሚደረጉ ትብብሮች ላይ ውይይት አደረጉ።
በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ እንዲሁም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው መሰረት የኃይል ፍላጎትን ከአቅርቦት ጋር ለማጣጣም የኒኩሊየር ኃይልን በአማራጭነት ለማበልፀግ እቅድ እንዳላትና በዝግጅት ላይ መሆኗንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ÷ ኒኩሊየርን ለአማራጭ ኃይል፣ ለካንሰር ሕክምና ምርምር እንዲሁም ለተለያዩ ዘርፎች ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ይበልጥ በቅርበት ለመስራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
የአለማቀፍ ኤጀንሲው የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር ዶክተር ሻውካት አብዱልረዛቅ በበኩላቸው ÷ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ኒኩሊየርን ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኃይል ማመንጨትና ለምርምር ዘርፍ ኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ማዋል እንድትችል የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን በኒኩሊየር ሕክምና ዘርፍ በጣሊያንና በጋና ከ6 እስከ 11 ወር የሚቆይ ስልጠና እንዲያገኙ እንደተደረገም አመላክተዋል።
በተመሳሳይም ሠላማዊ የኒኩሊየር ኃይልን ለዘላቂ ልማት በማዋል የሚገኘው ሁለንተናዊ ፋይዳ ላይ የተሻለ ግንዛቤ መጨበጥ እንዲቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ወደ ሞሮኮ ተልከው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መመቻቸቱንም ዳይሬክተሩ በውይይቱ አንስተዋል፡፡ ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በመጨረሻም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ትብብራቸውን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ሚዲያ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.