Fana: At a Speed of Life!

የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት አዴፓ፣ አብን እና የአምስቱ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጥምረት የያዘው የአማራ ድርጅት በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

በአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ አዘጋጅነት በአማራ ክልል እና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የአማራን ሕዝብ ማዕከል አድርገው የሚቀሳቀሱት አዴፓ፣ አብን እና የአምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የአማራ ድርጅት ከፍተኛ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈውበታል፡፡

ፓርቲዎቹ ከውይይታቸው በኋላ የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እና ጥቅሞች ምላሽ እንዲያገኙም በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በአማራ ክልል ብሎም በሀገሪቱ ሠላም፣ አንድነት እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበርም ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የአማራ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የሚደርስባቸውን በደል ለማስቆም እና መብትና ጥቅማቸዉ ለማስከበር ፓርቲዎቹ በጋራ ይሰራሉ፡፡

ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰዉ የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ዉድመት የተሰማቸዉን ጥልቅ ሐዘን ፓርቲዎቹ ገልጸው ለተጎጅ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የወንጀሉ ተሳታፊዎችም በሕግ እንዲጠየቁና ለተጎጅዎችም ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ጥሪ ማቅረባቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.