Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን አጽድቋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አስቸኳይ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ጉባኤ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በማድረግ ሾሟል።

ምክር ቤቱ ሹመቱን በሶስት ተቃውሞ፣ በ44 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው ያጸደቀው።

ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በማኔጅመንት እና ህዝብ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በክልላዊ እና አካባቢያዊ ልማት 2ኛ ዲግሪ እንዲሁም በልማት እና ጥናት 3ኛ ዲግሪ የትምህርተ ዝግጅት አላቸው።

ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪም እንዲሁም በአማራ ብሔራዊ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉና በተለይም በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ለሚገኙ መሪዎች ስልጠናዎችን በመስጠትና የስልጠና ሰነዶችን በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የቀረቡ የተለያዩ ሹመቶችን አጽድቋል።

በዚህ መሰረትም፦

• ዶክተር ሙሉነሽ አበበ – በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ

• ዶክተር ሰይድ ኑሩ – በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ

• ዶክተር ሲሳይ ዳምጤ-የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ

• አቶ ተፈራ ወንድማገኝ -የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ

• ዶክተር የሺመቤት መንግስቴ – የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር

• አቶ አቡዬ ካሳሁን- የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

• አቶ ሃይለየሱስ ተስፋማርያም -የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾመዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል የሠላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

በጉባኤው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ መላኩ አለበል እና የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋንታ ደጀን በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ኃላፊነት የተሰጣቸው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የሚገነዘብ እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር መስጠት እና ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለት ሹመት የተሰጣቸው የሥራ ሃላፊዎችም የተሻለ የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድ እና እውቀት እንዲሁም የአመራር ሙያ ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.