Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በምስራቅና ምእራብ ጎጃም ዞኖች የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በ2012 በጀት ዓመት በምስራቅና ምእራብ ጎጃም ዞኖች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀዋል።

በርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በምስራቅ ጎጃም ዞን 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው 403 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በዛሬው እለት መርቀው ከፍተዋል።

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ጌጠኛ (ኮብልስቶን) መንገዶች፣ ድልድይ እና ለመስኖ ልማት የሚውል ግድብ ይገኙበታል።

ከእነዚህም ውስጥ በማቻከል ወረዳ አበብ ደልማ ቀበሌ የተገነባው የመስኖ ግድብ አንዱ ሲሆን፥ 25 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል እና 155 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል መሆኑም ታውቋል።

በተያያዘ በአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በምእራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳና ቡሬ ከተሞች በ2012 በጀት ዓመት የተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶችን መርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱና በልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት ላይ የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌውም ተሳትፈዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በትናነትናው እለት በወምበርማ ወረዳ ከነበራቸው ቆይታ በመቀጠል የቡሬ ከተማ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል፤ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋርም ተወያይተዋል።

ቡሬ ከተማ ባለ ሃብቶች ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚያፈስሱባት በመሆኗ ተጨማሪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እንደሚያስፈልግ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረትም ለኢንቨስትመንቱ ፈተና እየሆነ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

ለከተማዋ ተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ እና የዩኒቨርሲቲ “ይገንባልን” ጥያቄም አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው አካባቢው በግብርና ምርታማነቱ የታወቀና የኢንቨስትመንት ትኩረትን የሳበ መሆኑን አንስተዋል።

ከከተማዋ እድገትና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር የሚጣጣም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እንዲገነባም ጥረት እናደርጋለን ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

የሃይል አቅርቦት እጥረቱን ለመፍታት በአካባቢው “ሰብ ስቴሽን” መገንባት እንዳለበት እንደታመነበት በመግለጽም ተግባራዊ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር በትብብር እንሰራለን ማለታቸውን የአብመድ ዘገባ ያመለክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.