Fana: At a Speed of Life!

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለይቶ በመደገፍና ክትትል በማድረግ የውጭ ንግድ ገቢውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 22፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለይቶ በመደገፍና ክትትል በማድረግ የውጭ ንግድ ገቢውን ለማሳደግ እየተሰራ  መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል÷ከክልል፣ከተማ አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የዘርፉን የ2012 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በጋራ በገመገሙበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ የተቋቋሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን አጠቃላይ መረጃ በማደራጀት የእያንዳንዱን ችግር በመለየት ችግሩ የሚፈታበትን ስልት በመቀየስ ዘርፉ የሚመለከተው ሁሉ በጋራ በመስራት  ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከዚያም ባለፈ ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ማመቻቸትና የቅርብ ክትትል በማድረግ የምርት አቅምን በማሳደግ ጥራትና ተወዳሪነትን በማሻሻል እንዲያመርቱ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ማዕቀፉ ለውጭ ባለሃብቶች ትኩረት በመስጠት ለሀገር ውስጥ ባሀብቱ የሚሰጠው ድጋፍ ዝቅተኛ የነበረ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን በማበረታታት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለኑሮ ውድነት ፣ላልተገባ የዋጋ ንረትና የወጭ ንግድ ገቢ መቀነስ የምርት አቅርቦት እጥረትና የጥራት መውረድ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉም ነው የተባለው ፡፡

ሚኒስትሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለችግር የማይበገር ተቋም በመመስረት ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በቅርበት በመነጋገር፣ ከራስ ጥቅም በዘለለ ተቋማቸው ለሀገር ብልፅግና የሚጫወተውን ሚና በመረዳት የምርት ጥራትን በማሻሻል በሁለትና ሶስት ሽፍት በመስራት ታሪክ የማይረሳው ኢኮኖሚያዊ አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.