Fana: At a Speed of Life!

የአረፋ በዓልን ስናከብር ራሳችንን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመጠበቅ ሊሆን ይገባል- ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልአድሃ በዓልን ሲያከብር ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከሆነው የኮሮናቫይረስ ራሱን በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በነገው ዕለት የሚከበረውን የአረፋ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ እና ለኮቪድ-19 ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዶክተር ሊያ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በቤቱ ሆኖ ማሳለፍ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በአስገዳጅ ሁኔታ ለገበያና ለሌላ ጉዳይ ከቤቱ የሚወጣ ከሆነ ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ ከማህበራዊ መስተጋብር ጋር ተያይዞ በኮቪድ-19 የሚያዘው ሰው ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል።

ወረርሽኙ ሰው የሚሰባሰቡበት እና ያልተገደበ እንቅስቃሴ በሚበዛበት ቦታ ስርጭቱ ስለሚጨምር ህዝበ ሙስሊሙ ጥንቃቄን እንዳይዘነጋ አስገንዝበዋል።

እንደ እምነት አባቶች ሁሉ የመጣብንን ፈተና በትዕግስትና በጥንቃቄ በማለፍ አርዓያነታችንን ለትውልድ ማትረፍ አለብንም ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ በወረርሽኙ ሳቢያ ለችግር የተዳረጉ ዜጎችንም በማሰብ ሊሆን እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በዓሉን አስመልክተው ከቦታ ወደ ቦታ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችና የግብይት ሥርዓት የሚፈጽሙ ሰዎች ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳስበዋል።

በአገሪቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15 ሺህ እንደተሻገረ ጠቅሰው፤ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.