Fana: At a Speed of Life!

የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ሁከት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ መርማሪ ቡድን ምርመራ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ሁከት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ መርማሪ ቡድን ከዛሬ ጀምሮ ወደየ አካበቢዎቹ በማቅናት ምርመራውን እንደሚያካሂድ ተገለጸ።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት እንዳስታወቀው፥ ወንጀሎቹን ለማጣራትና ለመመርመር ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ከክልሉ አቃቤ ህግ ጋር በመሆን ምርመራውን የሚያካሂድ መርማሪ ቡድን ተቋቁሟል።

ከዚያም ባለፈ ህዝብን ከህዝብ፣ ብሄርን ከብሄርና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት በሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ላይ ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል።

በመሰል ወንጀል የተጠረጠሩ የኦ ኤም ኤን፣ የአስራትና የድምጸ ወያነ ጣቢያዎች ላይ ከተወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ጣቢያዎቹ በወንጀል እንደሚጠየቁ ተነግሯል።

በትላንትናው ዕለትም በሶስቱ ጣቢያዎች የአዲስ አበባ ስቱዲዮዎች ብርበራ የተደረገ ሲሆን፥ የተገኙ ማስረጃዎች መኖራቸውም ተጠቁሟል።

የተገኙት ማስረጃዎች ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ይኑራቸው አይኑራቸው በቀጣይ በሚደረግ ምርመራ እንደሚረጋገጥም በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ መንግስት በቁርጠኝነት ህግ እንደሚያስከብር የተናገሩት ዳይሬክተሩ የትኛውንም አይነት ወንጀል የፈጸሙ አካላትን እንደማይታገስም አስታውቀዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.