Fana: At a Speed of Life!

የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ሊያደርግ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የግሉ ዘርፍ ሰራተኛውም ሆነ አሰሪም በተሰማራሩበት የሙያ ዘርፎች ውጤታማ በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ሊያደርግ ይገባል ተብሏል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ ከአሰሪና ሰራተኛ ማህበራት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በጋራ ውይይቱ አቶ መለሰ አለሙ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን የሚሆነው መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ተቋማትና አጠቃላይ ህዝቡ የድርሻውን ሲወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግና ሁሉን አሳታፊ የሆነውን ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።

አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ህዝብን የሚያፍኑና የሚበዘብዙ የህግ ማዕቀፎች ደረጃ በደረጃ በሂደት እየተሻሻሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ተቋማዊ አሰራርን በመከተል የሰራተኛው ዘላቂ ጥቅም እንዲረጋገጥ ያመላከቱት ሀላፊው ሰራተኛውም አሰሪውም በተሰማራበት ውጤታማ በመሆን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዓለም አቀፍ ቀውስ ባስከተለው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እንዳይዘጉ ሰራተኛው በፈረቃ እንዲሰራ መደረጉ፣ ሰራተኛውና አሰሪው በደንብ እንዲተዋወቅ የሙከራ ቅጥር ከ45 ቀን ወደ 60 ቀን ማደጉ ተነስቷል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰራተኛ ደህንነት መከታተያ ቴክኖሎጂ ለመተግበር እየተደረጉ የሚገኙ እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

የሰራተኛውን ጥቅም የሚጋፉ የሰራተኛና የአሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠር 40/60 የሚለውን 20/80 አድርጎ በማሻሻል የወጣው አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

ሰራተኛው ተደራጅቶ መብቱንና ጥቅሙን በማስከበር ሀገራዊ ለውጡን ዳር ለማድረስ ለሀገሩ በቅንነት እንደሚረባረብም የውይይቱ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በኤጀንሲዎች ላይ የሚስተዋለውን ውዝፍ ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍና 20/80 የሚለውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከውይይቱ በኃላም የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአሰሪና ሰራተኛ ማህበራት ተቀናጅቶ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የስምምነት ፊርማ መፈራረማቸውን ከአዲስ አበባ ፕረስ ስክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.