Fana: At a Speed of Life!

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለመስጠት የሚያግዝ አገር አቀፍ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት የሚያግዝ አገር አቀፍ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄደ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ኡስታስ አቡበከር አህመድ ፥ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጠናው ጥናት ለውሳኔ ከመቅረቡ በፊት ህዝቡ በስፋት ይወያይበታል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሪነት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላለፉት 18 ወራት የተካሄደው ጥናትና የውሳኔ ምክር ሃሳብ ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ ለውይይት መቅረቡንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ኡስታስ አቡበከር የገለጹት።
በአስተዳደር ወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ችግሮችና ጥያቄዎች በጥናቱ በጥልቀት መዳሰሳቸውንም አውስተዋል፡፡
የችግሮች አነሳስና ዕድገት በሀገራዊ ፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ሁለንተናዊ ሁኔታ ላይ ያለውን አንደምታ የዳሰሰ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምሩ ስራ ላይ ተጨማሪ ግብዓት ለመሰብሰብ በድሬዳዋ የመጀመሪያው ውይይት መደረጉን ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፥ ኮሚሽኑ በተሰጠው ሥልጣን በክልሎች የአስተዳደር ወሰን ፣ራስን በራስ የማስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎችን ሀገራዊ በሆነና በማያዳግም መንገድ ለመፍታት ለተደረገው ጥናት ተጨማሪ ግብዓት ለማግኘት ውይይት መደረጉ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ለአለመረጋጋት መንስኤ በመሆናቸው፥ ለችግሮቹ ገለልተኛ በሆነ ከፍተኛ የሙያ ብቃት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ያካሄደው ሀገር አቀፍ ጥናት መሠረታዊ ተግባር መሆኑን አስታወቀዋል፡፡
በክልሎች መካከል ለሚነሱ የወሰን ውዝግቦችና የማንነት ጥያቄዎች ለብዙ ደም መፍሰስና ሰብዓዊ ቀውሶች መነሻ በመሆናቸው፥ ኮሚሽኑ መንስኤያቸውን በሣይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ አማራጭ ሃሳቦችን ለውሳኔ ማዘጋጀቱ ወሳኝ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በውይይቱ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ የህብረተሰብ ባመሪዎች ፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.