Fana: At a Speed of Life!

የአስተዳደር ወሰን መካለሉ የሕዝብን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የአስተዳደር ወሰን የማካለል ሥራ የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና ዘላቂ ሰላም የሚያጠናክር መሆኑን ተናገሩ፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ባለመኖሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ቅሬታ ሲነሳ መቆየቱን አስታውሰው÷ ይህም ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግስት የልማት ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት÷ የወሰን ማካለል ሥራ መከናወኑ በሁለቱም ወገን የልማት ሥራዎች በተቀላጠፈ መልኩ እዲከናወን ያግዛል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው÷ አስተዳደራዊ ወሰንን የማካለሉ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከተማ ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ÷ የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደራዊ ወሰን መካለሉ የሁለቱን ወገን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
የአስተዳደር ወሰን ሥራው የኢፌዲሪ ሕገ መንግስትን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተርን እና የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥትን መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን አመራሮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የወሰን ማካለል ሥራው÷ የአስተዳደራዊ ሥራዎችንና የጋራ ልማትን በተሳለጠ መልኩ ለማስኬድ የሚያግዝና የአካባቢውን ነዋሪዎች የጋራ እሴት እንደሚያጠናክርም አመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.