Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሥራውን በይፋ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ሥራውን በይፋ ጀምሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ቦርዱን በይፋ ሥራ ሲያስጀምሩ እንዳሉት ይህ ቦርድ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ በመሆኑ በማንኛውም ጊዜ በሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚቋቋም ቦርድ ይለያል።

ከዚህ ባለፈም የዜጎችን ህይወት ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የተቋቋመ በመሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋልም ነው ያሉት።

ቦርዱ ይህን በመረዳት በከፍተኛ ሃላፊነትና ቁርጠኝነት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው ከቫይረሱ ተለዋዋጭነት ባህሪ አንፃር የቦርዱን ሥራ ተለዋዋጭ ሊያደርገው እንደሚችል ታሣቢ በማድረግ የቦርዱ አባላት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፈጣን የሆነ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአዋጁን ዝርዝር አፈፃፀም ደንብ አተገባበሩን በመከታተል፣ በሚቆጣጠርና እንደ አስፈላጊነቱ የማስተካከያ ሃሳቦችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርጋልም ብለዋል።

በተጨማሪም የአዋጁን ዝርዝር አፈፃፀም ደንብ ከህገ መንግስቱ አንፃር ክልከላ የተደረገባቸውን መብቶች ተገቢነታቸውን በጥልቅ በመመርመር ተፈፃሚነታቸውንም መከታተል እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ቦርዱ የአዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል ይረዳው ዘንድ የአፈፃፀም እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን፥ በእቅዱ የነፃ የሥልክ ጥሪ ማዕከል፣ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችን መፍጠር እና ርቀትን ጠብቆ በሚደረግ የገጽ ለገጽ ምልከታ የወረርሽኙ ስርጭት ያለበትን ደረጃ ከህብረተሰቡ ጋር መረጃ መለዋወጥ የሚችልበትን መንገድ አመላክቷል።

የቦርዱ አባላትም የተሰጣቸውን ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.