Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪውን ቡድን አከርካሪ የሰበረው መከላከያ ሃይል የትኛውንም ጠላት መደምሰስ የሚችልበት አቅም ገንብቷል- ጀነራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ጥር 12፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን የማፈራረስ አላማ ይዞ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን አከርካሪ የሰበረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሃይል የትኛውንም ጠላት መደምሰስ የሚችልበት አቅም መገንባቱን የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ተናገሩ።
የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፥ በድል የተጠናቀቀውን “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” አስመልክተው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር አድርገዋል።
የኢትየጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጠላቶች በጋራ በመሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት በማፍረስ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ጫፍ ደርሰው እንደነበር ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ሀይሎች የሽብር ቡድኑን የሚያግዝ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማዘጋጀት፣ የሽግግር መንግስት በማቋቋም እና የስልጣን ክፍፍል በማድረግ፣ የሸኔ ቡድን የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዲያሳካ እድል በመስጠት ሀገሪቱን ለመከፋፈል እና ህልውናዋን ለማዳከም የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ተነስተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመራው “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” የኢትዮጵያ ጠላቶች ያሰቡትን እንዳያሳኩ በማድረግ ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ መቻሉንና ሀገርን ከብተና መታደግ መቻሉን ምክትል ኢታማዡር ሹሙ ተናግረዋል፡፡
የዘመቻው አንዱ ግብ አሸባሪውን የህዋሃት ቡድን አከርካሪ መስበር ነበር ያሉት ጄኔራሉ፥ ይህንን እቅድም በሽብር ቡድኑ ላይ በመፈፀም በወረራ ይዟቸው ከነበራቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ጠራርጎ ማስወጣት ተችሏል ብለዋል፡፡
አሸባሪው የህዋሃት ቡድን ይዟቸው የነበሩትን የአየር መቃዎሚያዎች፣ ታንኮች እና ከባድ መሳሪያዎችን እንዲሁም ለረዠም ጊዜ የሰበሰባቸውን ከፍተኛ የጦር አመራሮቹን በጦርነቱ አጥቷል ብለዋል ምክትል ኢታማዡር ሹሙ፡፡ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይቻል ከልቡ ተምሯልም ብለዋል።
መከላከያ ሰራዊት ለምን ወደ ትግራይ አልገባም ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጄኔራሉ በሰጡት ማብራሪያ፥ የመከላከያ ሰራዊት ባለበት እንዲጸና የተደረገው የመጀመሪያው ምእራፍ ዘመቻ በመጠናቀቁ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያ ምእራፍ ተጠናቀቀ ማለት ሁለተኛ ምዕራፍ አለ ማለት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፥ ሰራዊቱ የትኛውንም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
መቀሌ እና ትግራይ የኢትዮጵያ ግዛት ናቸው፤ ስለሆነም አስፈላጊ በሚሆንበት ሰዓት ሰራዊቱ ገብቶ ጠላትን ከመደምሰስ የሚያቆመው ሀይል የለም ብለዋል፡፡
ጀነራል አበባው ታደሰ፤ የመጀመሪያ ምእራፍ ዘመቻውን ያጠናቀቀው መከላከያ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ለየትኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆኑንና ለዚያም በሚያስፈልገው አስተማማኝ አቋም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ለመከላከያ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት የተሰጠውን የማእረግ እድገት እና የሜዳይ ሽልማት በተመለከተም ሲያብራሩ፥ ሽልማቱ ስራ እና ስራን ብቻ መስፈርት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጀነራሉ ሲያስረዱ፥ “እንደመከላከያ ጠንካራ ቡድን ነን፤ እንደሰው ነው ምንሄደው፤ በስራ ነው የምንለካው” ብለዋል።
ብሄር በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሸልማትም ሆነ የማእረግ እድገት መስፈርት እንዳልሆነ የተናገሩት ጀነራል አበባው፥ ሸልማትም ሆነ የማእረግ እድገት ያገኙት ሁሉም የጦር መኮንኖች ይገባቸዋል ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ በሸልማትም ሆነ የማእረግ እድገቱ ደስተኛ መሆኑን በማንሳት በሰራዊቱ ውስጥ ብቃት እና ጀግንነት እንጂ ብሄር አይቆጠርም ብለዋል።
ከጀነራል አበባው ታደሰ ጋር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደረገው ሙሉ ቃለ መጠይቅ ነገ አርብ ምሽት በሁሉም የቴሌቪዥንና የዲጂታል ሚዲያ ማሰራጫዎቻችን የምናቀርብ ይሆናል።
በዳዊት መስፍን
ይህንን ዜና በምስል ለመመልከት ሊንኩን ይጫኑ https://www.youtube.com/watch?v=c9PY6bOw
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.