Fana: At a Speed of Life!

የአበባ እርሻ ልማት ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር መፍጠር እንዳለባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ኩባንያን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ባቱ፣ አዳሚቱሉ እና ቆቃ አካባቢዎች 650 ሄክታር መሬት ላይ የአበባ ምርትን በማምረትና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የሚታወቀው ሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ለአካባቢው ማህበረሰብ እየሰጠ ያለውን ማህበራዊ አገልግሎት ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል፡፡
በምልከታውም ኩባንያው ለ12 ሺህ 865 የሰው ኃይል የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አበራ ማሞ እንዳሉት÷ የልማት ማህበሩ በዋናነት ከተሰማራበት የአበባ ምርትን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሁም በውስጡ ለሚሰሩ የሰራተኞች ልጆች ሙሉ በሙሉ ከክፍያ ነጸ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ማህበሩ በራሱ ወጪ ያስገነባው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች የሚያዘወትሩበት፣ ህዝባዊ ስብሰባዎችንና በዓላትን የሚያስተናግድ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አስገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ ኩባንያው አካባቢውን ከአበባ እርሻ ጣቢያው ከሚለቀቅ የኬሚካል ብክለት ለመከላከልና ሀገሪቱ ለያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ ስኬት ሲባል ስነ-ህይወታዊ የተባይ ማጥፊያ ዘዴዎችን ከመጠቀም ባሻገር ከእርሻ የሚወጣ ማንኛውንም አይነት ፍሳሽ በተገጠመለት ዘመናዊና ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ ዘዴ ተጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አስረድተዋል፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ኩባንያው 350 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመበት ጠቁመው በተፈጠረው ሁኔታ የአካባቢው ማህበረሰብ ኩባንያውን መልሶ በመገንባቱ ወደ መደበኛ ስራው ተመልሷል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ኢታፋ ዲባ በበኩላቸው ÷ ኩባንያው ለሃገሪቱ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ እና በውስጡ ለሚሰሩ ባለሙያዎች የህክምና፣ የትምህርት እና በመዝናኛው ዘርፍ እየሰጠ ያለው ማህበራዊ አገልግሎት እንዳስደሰታቸውና ተጠናክሮ ሁኔታው መቀጠል አለበት ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.