Fana: At a Speed of Life!

የአቢጃታ ሐይቅ ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለሱን የአብጃታ ሻላ ሃይቆች ብሄራዊ ፓርኮች አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጥፋት ስጋት ላይ የነበረው የአቢጃታ ሐይቅ በክረምቱ ዝናብ ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለሱን የአብጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ አስታወቋል።

ከኦሮሚያ የመስህብ ስፍራዎች አንዱ የሆነው የአቢጃታ ሐይቅ ትናንት በባለድርሻ አካላት የተጎበኘ ሲሆን ጉብኝቱ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በክልሉ ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተነግሯል ።

የብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡዳሞ 192 ካሬ ኪሎ ሜትር የነበረው የሐይቁ ስፋት በሰው ሰራሽ ምክንያት በመድረቁ ወደ 54 ካሬ ኪሎ ሜትር ወርዶ የነበረ ሲሆን ከፋብሪካ የሚለቀቅ ሶዳ አሽ የተሰኘ ኬሚካል በሐይቁ ላይ ባደረሰው ጉዳት አዕዋፋትና አሳዎች ጠፍተው እንደነበር አስታውሰዋል ።

ባለፈው ክረምት በነበረው ዝናብ በስፍራው ላይ ውሀ በመሙላቱ የሐይቁ ይዞታ ወደ 132 ካሬ ኪሎ ሜትር መመለሱን የተናገሩት ሃላፊው በሐይቁ ስፍራ ጠፍተው የነበሩ ስደተኛ ወፎችና የዱር እንስሳትም መመለሳቸውን ገልጸዋል ።

በተለይም የፍላሚንጎ ዝርያ ያላቸው ስደተኛ ወፎች እንዲሁም አሳዎች ተመልሰው ሐይቁ የቀድሞውን ይዘት መያዙን ተናግረዋል።

ስፍራው ለጎብኚዎች ተመልሶ የተከፈተ መሆኑን በመግለጽም በመንከባከብና በመጎብኘት የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.